ጆ ባይደን ቢሮ ውስጥ ስለተገኘው ምሥጢራዊ ሰነድ ሪፐብሊካኖች ምርመራ ሊጀምሩ ነው  

ታትሟል

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቀድሞ ቢሯቸው ውስጥ ተገኘ ስለተባለው ጥብቅ አገራዊ ምሥጢራዊ ሰነድን በተመለከተ ሪፐብሊካኖች በፕሬዝዳንቱ ላይ ምርመራ እንደሚጀምሩ ዛቱ።

ይህ ‘ጥብቅ የአገር ምሥጢር’ ተብሎ የተቀመጠው ሰነድ የተገኘው ጆ ባይደን ቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ ይጠቀሙበት በነበረ አንድ ቢሮ ነው።

በቁጥር ዐሥር ይሆናሉ የተባሉት ሰነዶችን በአጋጣሚ የቢሮ ዕቃዎች ሲዘዋወሩ ነው የተገኙት ተብሏል።

ሰነዶቹን ያገኟቸው ደግሞ የጆ ባይደን የግል ጠበቆች ናቸው። በሰነዶቹ “የግል” የሚል ተጽፎባቸው ነው የተገኙት።

ይህን ተከትሎ የታችኛው ምክር ቤትን የሚቆጣጠሩት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል እንደራሴዎች ጆ ባይደን ላይ ምርመራ እንዲከፈት እናደርጋለን’ ሲሉ ዝተዋል።

በአሜሪካ ሕግ ‘ጥብቅ የአገር ምሥጢር’ የተደረጉ ሰነዶች መቀመጥ የሚችሉት በፌዴራል ቤተ-መዘክር ውስጥ ብቻ ነው።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲህ ያሉ “ጥብቅ የአገር ምሥጢር” ተብለው ማኅተም ያረፈባቸው ሰነዶችን ከሥልጣን ሲወርዱ ወደ ፌዴራል ቤተ መዘክር መመለስ ሲኖርባቸው እርሳቸው ግን ወደ ቤታቸው ይዘው በመሄዳቸው ጉዳያቸው በልዩ ፍርድ ቤት እየተመረመረ ነው።

እነዚህ በዶናልድ ትራምፕ የፍሎሪዳ ማሮላጎ መኖርያ ቤት በፖሊስ በድንገተኛ ፍተሻ የተገኙት ሰነዶች 300 ይሆናሉ።

በወቅቱ ጆ ባይደን ስለጉዳዩ ተጠይቀው “ድሮም ዶናልድ ትራምፕ ኃላፊነት የማይሰማው ከንቱ ሰው ነው” ሲሉ ወርፈዋቸው ነበር።

ይሁንና ጆ ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ ያዘወትሩት የነበረው ቢሯቸው ውስጥ በተመሳሳይ “ጥብቅ የአገር ምሥጢር” እንደሆኑ ማኅተም የተደረገባቸው ሰነዶች መገኘታቸው ጆ ባይደንን ‘ግብዝ’ ያሰኛቸው ሲሆን በአንጻሩ ትራምፕን እና ሪፐብሊካኖችን አስፈንድቋል።

ዜናው እንደተሰማ ትራምፕ ራሳቸው በፈጠሩት ‘ሶሻል ትሩዝ’ በሚባለው ማኅበራዊ ገጽ ላይ በጻፉት አስተያየት “ለምንድነው ፌዴራል ፖሊስ እኔና ባይደንን በእኩል የማይፈትሸን፤ የጆ ባይደን ቤት አሁኑኑ መፈተሽ አለበት፤ ዋይት ሃውስ ፖሊስ ብርበራ ያድርግ’ ሲሉ ጽፈዋል።

ጎረቤት ሜክሲኮ የሚገኙት ጆ ባይደን በበኩላቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት “ስለ ጉዳዩ ስሰማ እኔም ተደንቂያለሁ” ብለዋል።

ጨምረውም ስለ ሰነዶቹ ምንም እንደማያውቁ፣ ጠበቆቻቸውም ስለ ይዘቱ እንዳይጠይቁ፣ እርሳቸውም ከፍተው እንዳያነቧቸው እንደከለከሏቸውና ሰነዶቹ ቢሮ ወስጥ በተገኙ ጊዜም ጠበቆች ወዲያውኑ ለፌዴራል ቤተ መዘክር ስልክ ደውለው በነገታው ወደዚያው እንደተወሰዱ አብራርተዋል።

እነዚህ ጥብቅ ምሥጢር ሰነዶች በውስጣቸው ስለ ኢራን፣ ስለ ዩክሬንና ስለ ዩኬ ሕዝብ ማወቅ የሌለበትን ቁልፍ መረጃዎችን ይዘዋል ይባላል።

ጥብቅ ምሥጢር የያዙት ሰነዶች እንዴት የባይደን የቀድሞ ቢሮ ሊገኙ እንደቻሉ ለጊዜው ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ሰነዶቹ የተገኙበት ቢሮ “ፔን ባይደን ሴንተር” ውስጥ ሲሆን ይህን ቢሮ ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ አዘውትረው ይጠቀሙበት ነበር ተብሏል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ቴሌቪዥን በደረሰ ሌላ መረጃ እነዚህ ጥብቅ ምሥጢር የተደረጉ ሰነዶች በውስጣቸው የኒክሊየር ምሥጢርን የያዙ አይደሉም።

ሰነዶቹ በባይደን ጠበቆች በድንገት የተገኙት በኅዳር የአጋማሽ ዘመን የመዳረሻ ምርጫ (midterm elections) ከመጀመሩ በፊት ነው።

ነገር ግን ዜናው የወጣው እጅግ ዘግይቶ አሁን ነው።

ዶናልድ ትራምፕን ያበሳጨው ሌላው ነገር ለምን ይህ መረጃ ከምርጫው በፊት ለሕዝብ ይፋ እንዳልተደረገ ነው።

ይህ ጉዳይ ወትሮም እየተቃቃሩ አብሮ መሥራት የተቸገሩትን የሪፐብሊካንና የዲሞክራት ፓርቲዎችን ይበልጥ የሚያባላ ጉዳይ ሊሆን ይችላል ይላሉ ተንታኞች።