ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስድስት ወራትን ያስቆጠረው የጋዛ ጦርነት አሃዛዊ መረጃዎች
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ወር በጋዛ “አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ሁሉም ታጋቾች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እስረኞችን እንዲፈቱ” ጠይቋል። ነገር ግን ለወራት የዘለቀው የቦምብ ጥቃት ግን የመቀነስ ምልክት አላሳየም። የሟቾች እና የአካል ጉዳቶች ቁጥርም እየጨመረ ነው።
ጦርነቱ በጋዛ ሰርጥ ያለውን የመሠረተ ልማት አውታር ወደ ፍርስራሽነት ቀይሮታል። ነዋሪዎቿ ወደ ደቡብ ወደ ራፋህ ከተማ እንዲወጡ ተገደዋል። ይህም የረሃብ አደጋ ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል ሲል በተባበሩት መንግስታት የሚደገፍ ሪፖርት አስጠንቅቋል።
ጦርነቱ የተቀሰቀሰው መስከረም 26 ሐማስ ታይቶ የማያውቅ የተባለለትን ጥቃት እስራኤል ውስጥ መፈጸሙን ተከትሎ ነው። በጥቃቱ 1200 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን እስራኤል አስታውቃለች።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ኅብረት ሐማስን አሸባሪ ሲሉ ፈርጀዋቸዋል።
በጥቃቱ ወቅት 253 ሰዎች ታግተዋል። 130 የሚደርሱ ታጋቾች አሁን ድረስ ጋዛ ውስጥ ይገኛሉ ተብሎ ይታመናል። 34 የሚሆኑት ግን ሳይሞቱ እንዳልቀረ የእስራኤል ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ከመስከረም 26 ወዲህ ቢያንስ 600 የእስራኤል ጦር አባላት ተገድለዋል። 256 የሚሆኑት ተገደሉት በጋዛ ሰርጥ የምድር ጦሩ ዘመቻ ከጀመረ በኋላ ነው።
ጦርነቱ ከተከፈተ እስከ 175ኛው ቀን ድረስ ቢያንስ 32 ሺህ 623 ሰዎች ሞተዋል። ከ75 ሺህ በላይ ቆስለዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አስታውቋል።
በጋዛ ሰርጥ የሚገኘው እና በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከሆነ፣ 178ኛው ቀን ድረስ ቢያንስ 32 ሺህ 916 ሰዎች ተገድለዋል። አብዛኞቹ ደግሞ ሴቶች እና ህጻናት ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአንድ ወር በፊት ባወጣው ዘገባ መሠረት 9 ሺህ የሚገመቱ ሴቶች ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል ብሏል። እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በርካታ አስከሬኖች ከፍርስራሾች ስር ባለመውጣታቸው ይህ አሃዝ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ይታሰባል።
የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በበኩሉ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ከ13 ሺህ በላይ ህጻናት በጋዛ ተገድለዋል ብሏል።
እንደ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ያሉ አንዳንድ ፖለቲከኞች የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር የሚያቀርበው ቁጥር ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ነበር። የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ቁጥሩ አስተማማኝ ነው ብሎ ያምናል ።
“አሰቃቂ” የምግብ እጦት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው ከሆነ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው ሕዝብ 85 በመቶ የሚሆኑት በጋዛ ሰርጥ ባለው ጦርነት ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ተገደዋል።
የረሃብ መጠንን በመለካት መረጃ የሚያወጣው የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (አይፒሲ) የተባለው ተቋም፣ በጋዛ የማይቀር ረሃብ አንዣቧል ሲል ባለፈው ወር አስጠንቅቋል።
“የምግብ ዋስትናን በተመለከተ ከጋዛ ሰርጥ ግማሽ ያህሉ ሕዝብ (1.11 ሚሊዮን ሰዎች) አስከፊ ሁኔታ ይገጥማቸዋል ተብሎ ይጠበቃል” ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምገማ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ እንደያዘ እስራኤል ገልጻለች። የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት በየቀኑ የሚመጣውን እርዳታ ማሰራጨት እንዳልቻሉ አክላለች።
በእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር የሲቪል ጉዳዮች ማስተባበሪያ ክፍል (ኮጋት) “በኬሬም ሻሎም መተላለፊያ ላይ በእስራኤል ባለሥልጣናት ሙሉ በሙሉ ፍተሻ የተደረገባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪናዎች በጋዛ ቆመዋል” ብሏል።
“እስራኤል በጋዛ ሲቪል ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጦርነት አሳዛኝ ውጤት ታውቃለች” በማለት አክሎ እስራኤል ሆን ብላ የጋዛ ነዋሪዎችን እያስራበች ነው የሚለውን ውንጀላ ግን ውድቅ አድርጋለች ጓል።
ወደ ጋዛ የሚያስገባውን መሸጋገሪያ በመክፈት እና ወደ ግዛቱ የሚደረገውን የእርዳታ ፍሰት እንዲፋጠን የሚቀርቡ ጥሪዎች ጨምረዋል። እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ከሆነ ከጦርነቱ በፊት በየቀኑ ቢያንስ 500 የጭነት መኪናዎች ወደ ጋዛ ሲገቡ ነበር።
በጋዛ ውስጥ ትልቁን የእርዳታ ድጋፍ ሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ኡንርዋ እንዳለው ከሆነ በመጋቢት ወር በየቀኑ በአማካይ 161 የጭነት መኪናዎች ይገቡ ነበር።
እስራኤል በበኩሏ በጋዛ ሰርጥ ሊገባ በሚችለው የሰብዓዊ እርዳታ መጠን ላይ ምንም ገደብ አላስቀመጥኩም ብላለች ።
የጋዜጠኞች እና የእርዳታ ሠራተኞች ግድያ
እንደ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን (አይኤፍጄ) ከሆነ፤ 99 የፍልስጤም ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለሙያዎች፤ አራት እስራኤላውያን እና ሦስት የሊባኖስ ዜጎች ተገድለዋል።
በጋዛ ያለውን ጦርነት ሲዘግቡ የነበሩ 16 ጋዜጠኞች ቆስለዋል፣ አራቱ መጥፋታቸውን እና 25ቱ ደግሞ መታሰራቸውን ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ) ዘግቧል።
ከጋዛ ለመዘገብ የሚሞክሩ ጋዜጠኞች መግባት የሚችሉት ከእስራኤል ጦር ጋር አብረው በመሆን እና በጦር ኃይሉ የተደነገጉትን ቅድመ ሁኔታዎች ለማሟላት ከተስማሙ ብቻ ነው።
ይህም ከእስራኤል ወታደሮች ጋር መቆየትን እና ታሪኮችን ከማውጣታቸው በፊት ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) መደረግን ይጨምራል።
ከጥቅምት ወር ወዲህ በጋዛ ከ196 በላይ የረድኤት ሠራተኞች ተገድለዋል ሲል በእርዳታ ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ዋና ዋና ጥቃቶችን የሚመዘግበው እና በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ኤይድ ዎርከር ሴኪውሪቴ ዳታቤዝ አስታውቋል።
ከስድስት ወራት በፊት ከተቀሰቀሰው ጦርነት ወዲህ የተገደሉት አብዛኛዎቹ በጋዛ ትልቁን የእርዳታ ሥራ የሚያካሂደው ኡንርዋ ሠራተኞች ናቸው።
የምድር ዘመቻው ስጋት
ከሳምንታት በፊት ጀምሮ እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ በስተደቡብ በምትገኘው ራፋህ የምድር ዘመቻ እንደምትጀምር ስትዝት ቆይታለች።
አካባቢው ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን መጠለያ ሆኗል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ከሌሎች አካባቢዎች ተፈናቀለው የመጡ ናቸው።
መጠነ ሰፊ የእስራኤል ጦር ወደ ራፋህ ዘልቆ ከገባ “ከሚታሰበው በላይ” የሰብዓዊ ጥፋት ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን እንዲፈቱ ለማድረግ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እና ምርጫ ቀደም ብሎ እንዲካሄድ የሚጠይቁ ግፊቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ በርትቷል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በተደረገው ትልቁ የፀረ መንግሥት ሠላማዊ ሰልፍ፣ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን እየሩሳሌምን አጥለቅልቀዋል።
ተቃዋሚዎቹ በጦርነቱ አያያዝ ላይ ቅሬታቸውን ከመግለጽ ባለፈ መንግሥት ታጋቾችን ለማዳንም ሆነ ለማስፈታት አለመቻሉን ተችተዋል።