ኤርዶዋን እና ጉቴሬዝ ከዘሌንስኪ ጋር ለመነጋገር ኪዬቭ ገቡ

ታትሟል

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ለመነጋገር ኪዬቭ ገቡ።

ጉቴሬዝ፣ በደቡባዊ ዩክሬን በሚገኘው ዛፖሪዣ የኒውክሌር ማብላያ አቅራቢያ ውጊያ መካሄዱ “እጅግ እንዳሳሰባቸው” ተናግረዋል።

“ዛፖሪዚያ ላይ ማንኛውም ጉዳት ቢደርስ ራስን በራስ የማጥፋት ያህል ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዜሌንስኪ እና ጉቴሬዝ ከግንቦት ወዲህ ሲገናኙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው።

በወቅቱ ኪዬቭ በሮኬት መመታቷ ይታወሳል።

የዩክሬን ኒውክሌር ማብላያ አቅራቢያ የሚደረገው ውጊያ “ሌላ ቼርኖቤል” ሊያስከትል እንደሚችል የመንግሥታቱ ድርጅት ስጋቱን ገልጿል።

ሩሲያ አካባቢውን በቁጥጥር ሥር ካዋለች ወዲህ ከሰሞኑ በሞስኮ እና በኪዬቭ በኩል የከባድ መሣሪያ ድብደባ እየተፈጸመ ይገኛል።

ሩሲያ አካባቢውን ወደ ወታደራዊ መቀመጫ ለውጣለች ተብላ ትተቻለች።

በክሪሚያ አቅራቢያ በቤልቤክ ወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ ፍንዳታዎች እንደተሰሙ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

የሴቫስቶፖል ከንቲባ ሚካሂል ራዝቮዚሄይቭ በፍንዳታዎቹ የተጎዳ ሰው የለም ብለዋል።

ከሩሲያ ትዕዛዝ የሚቀበሉ ዩክሬናውያን የኒውክሌር ማብላያው ሠራተኞች የኒውክሌር ፍንዳታ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተደጋጋሚ የወታደራዊ ጥቃቶች ዒላማ እንደሆነም ገልጸዋል።

“እየሆነ ያለው ነገር አስፈሪ ነው። ኢ-ሞራላዊም ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

የዩክሬን መንግሥት መልዕክት የሚተላለፍበት የትዊተር ገጽ ላይ እንደተጻፈው፣ የኒውክሌር ማብላያው ባለፈው ሳምንት ባልተጠበቀ ሁኔታ አንድ ቀን ለሠራተኞቹ እረፍት ሰጥቷል።

“ሩሲያውያን በኒውክሌር ማብላያው ድንገተኛ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጁ እንደሆነ የዩክሬን የደኅንነት ምንጮች ይጠቁማሉ” ተብሏል።

ዜሌንስኪ ይህ ትዊት ከመሰራጨቱ በፊት “በሩሲያ ግድየለሽነት ምክንያት ዓለም ወደ ኒውክሌር ቀውስ ልታመራ ትችላለች” ብለዋል።

ቢቢሲ እነዚህን ክሶች ከገለልተኛ ወገን አላጣራም።

በዓለም ትልቁ የኒውክሌር ቀውስ ቼርኖቤል ሲሆን፣ የዩክሬን የኒውክሌር ማብላያ ግን ከቼርኖቤል በተሻለ የደኅንነት ጥበቃ ሥር እንደሚገኝ ይገለጻል።

ኒውክሌሩን የሚያስነሳው ቁልፍ በቀላሉ በሰው ሠራሸም ይሁን በተፈጥሯዊ ፍንዳታ እንደማይከፈት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሌላ በኩል ኤርዶዋን በዜሌንስኪ እና በቭላድሚር ፑቲን መካከል ውይይት ሊያመቻቹ እንደሚችሉ መረጃዎች ወጥተው ነበር።

ከፑቲን ጋር ቅርበት ያላቸው ኤርዶዋን ተዋጊ ኃይሎቹን ለድርድር ወደ ጠረጴዛ ማምጣት ከተቻለ ጦርነቱን ማስቆም እንደሚቻል ያምናሉ።

ዜሌንስኪ የኤርዶዋንን ጉብኝት ቢደግፉም አሸማጋይነታቸውን የሚቀበሉ አይመስልም።

“ሩሲያ ለሰላም ዝግጁ ናት” ብለው ኤርዶዋን ቢናገሩም፣ ዘለንስኪ ግን “ሩሲያን ማመን ይከብዳል” ብለዋል።