ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ጀርመን ኢራን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኢራን እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ በተቃዋሚዎች ላይ የኃይል እርምጃ በሚወስዱት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቁ።
አናሌና ባየርቦክ የአውሮፓ ኅብረት የግለሰቦቹ ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ እንዲያግድ እና ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ ጀርመን ትሠራለች ብለዋል።
“በመንገድ ላይ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን የሚደበድቡት ከተሳሳተ ታሪክ ጎን ነው የቆሙት” ሲል ገልጸዋቸዋል።
እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም. በማዕቀቡ ጉዳይ ተወያይተው ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ባየርቦክ ለአንድ የጀርመን ጋዜጣ ሲናገሩም “በነጻነት ከመኖር ውጪ ምንም የማይፈልጉትን ሰዎች በሞት እንዲቀጡ የሚጠይቁትን” ተችተዋል።
ለኢራናውያንም “ከእናንተ ጎን እንቆማለን። በዚሁም እንቀጥላለን” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የማህሳ አሚኒ ሕይውት ካለፈ በኋላ በኢራን ህዝባዊ ሰልፎችን በመቀስቀሳቸው ነው የማዕቀቡ ሃሳብ የመጣው።
የ22 ዓመቷ ወጣት መስከረም 16 በኢራን የስነምግባር ፖሊስ ከታሰረች በኋላ ሕይወቷ አልፏል።
የአሚኒን ግድያ ለመቃወም ወደ ጎዳና የወጡ በርካታ የሚቆጠሩ ኢራናውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።
መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን እንዳለው አለመረጋጋቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 19 ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 185 ሰዎች ተገድለዋል።
የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙሃን 20 የእስላማዊ አብዮት ጠባቂ አባላት፣ ፖሊሶች እና የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ዘግበዋል።
በሳምንቱ መገባደጃ ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተሰራጩ ቪዲዮዎች እና ምስሎች የኢራን የደኅንነት አባላት ወደ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ሲገቡ አሳይተዋል።
በቴህራን ዩኒቨርሲቲ ያሉ ሴት ተማሪዎች ቅዳሜ ዕለት በዩኒቨርሲቲው ጉብኝት ያደረጉትን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲን “ከዚህ ይጥፉ” ሲሉ ተደምጠዋል።
በተመሳሳይ ዕለት የሃገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተጠልፏል።
የቴሌቭዥን መስኮቶች ጭምብል እና የሃይማኖታዊው መሪ አያቶላ ካሜኒ ምስል በእሳት ተከቦ አሳይተዋል።
በርካቶች ኢራን ውስጥ የኢስላማዊ አገዛዝ እንዲያበቃ እየጠየቁ ነው።












