ሳዑዲ መንግስትን በማሕበራዊ ሚዲያ ተችተዋል ያለቻችውን አሜሪካዊ በ16 ዓመት እስራት ቀጣች

የፎቶው ባለመብት, IBRAHIM ALMADI
የሳዑዲ አረቢያ ፍርድ ቤት ሳድ ኢብራሂም አልማዲ የተባሉ አሜሪካዊ መንግሥትን የሚተች ጽሑፍ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርተዋል በሚል የ16 ዓመት እስራት እንዳስተላለፈባቸው ልጃቸው ለቢቢሲ ተናገረ።
የአሜሪካ እና የሳዑዲ አረቢያ ጥምር ዜግነት ያላቸው የ72 ዓመቱ አዛወንት ሳድ፤ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ከፍሎሪዳ ወደ ሪያድ ከተጓዙ በኋላ ነበር በህዳር ወር 2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋሉት።
በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየት ሰጥተው ከማያውቁት የሳድ ቤተሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ልጃቸው ኢብራሂም አልማዲ አባቴ በእስር ቤት ሲሞት መመልከት አልፈልግም ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
አባቱ በሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ከታሰሩበት ግዜ ጀምሮ በስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግሯል።
ቅጣቱን ያስተላለፈው የሳዑዲው ፍርድ ቤት፤ መንግሥትን ለማወክ ብሎም ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመርዳት ጥፋተኛ ሲል አዛውቱ ላይ ብይን አስተላልፏል።
ልጃቸው ኢብራሂም በበኩሉ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ብቸኛው ማስረጃ 14 ትዊቶችን የያዘ ሰነድ ነው ብሏል።
ቢቢሲ እነዚህን ትዊቶች የተመለከተ ሲሆን በመካ እና ጅዳ ከተሞች አሮጌ መንደሮች መፍረስን በመቃወም የጻፉት ጽሑፍ ይገኝበታል። እንዲሁም በሳዑዲ ያለውን የደኅንነት ስጋቶች እና የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂን ግድያ የሚመለከቱ ትችቶች ይገኙበታል።
ዐቃቤ ሕግ እስከ 42 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ጥያቄ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ከሁለት ሳምንት በፊት የ16 ዓመት ጽኑ እስራት እና ለ16 ዓመታት ደግሞ ጉዞ ማድረግ እንዳይችሉ እገዳ ጥሏል።
ኢብራሂም አባቱ ከታሰሩ ጀምሮ ሊያነጋግራቸው ባይችልም በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ የቤተሰቡ አባላት ግን ሳድን አግኝተው ማነጋገራቸውን እና በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ኢብራሂም ግን በዚህ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ለቢቢሲ ገልጿል።
ኢብራሂም የአሜሪካ መንግሥት በአባቴ ጉዳይ ላይ እርምጃ መውሰድ አልቻለም በሚልም ተችቷል። ከፍርዱ በፊት አባቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት ወኪሎች ሁለት ግዜ ብቻ እንዳናገሯቸው እና የመጀመሪያው ጉብኝታቸው አባቱ ከታሰሩ ከስድስት ወራት በኋላ የተካሄደ መሆኑንም አክሏል።
ኢብራሂም በአባቱ ጉዳይ ጫና እንዲያደርጉለት በማሰብ ዋይት ሀውስን በቀጥታ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ውድቅ እንደተደረገበትም ተናግሯል።
በነሃሴ ወር ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ሳዑዲ አረቢያ በተጓዙበት ወቅት ኢብራሂም የአባቱን ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቢቢሲ ይፋ አድርጎም ነበር።
አሜሪካ በአንድ ጉዳይ ሁለት አካሄድን ትከተላለች ያለው ኢብራሂም አንድ ዜጋ ሩሲያ ወይም ኢራን ውስጥ ሲታሰር አሜሪካ ጠንከር ያለ እርምጃ ብትወስድም ይህ ግን በሳዑዲ አረቢያ ላይ በተመሳሳይ ሲተገበር አይታይም ሲል ተችቷል።
"ሀቢቢ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ከታሰርክ ከአንተ አንድ የነዳጅ በርሜል ይበልጣል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ያሉ አንድ ምንጭ ፕሬዝዳንት ባይደን በሳዑዲ በነበራቸው ቆይታ የሳድን ጉዳይ አንስተው እንደሆነ ሲጠየቁ አገራቸው በውጪ የሚገኙ ዜጎቿን ከመጠበቅ የዘለለ ሃላፊነት የለባትም ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረባ ለዋሽንግተን ፖስት በሰጡት መረጃ የባይደን አስተዳደር የሳድን ጉዳይ ከሳዑዲ መንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር አንስተው መወያየታቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ኢብራሂም የአሜሪካ ባለስልጣናት ለአባቱ ምንም አይነት ሀዘኔታ አላሳዩም በሚል ተችቷል።












