ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የታይላንድን ዘውዳዊ ሥርዓትን አንቋሿል የተባለው የ50 ዓመት እስር ተፈረደበት
የታይላንድ ፍርድ ቤት የአገሪቱን ዘውዳዊ ሥርዓት ስም አጠልሽቷል በተባለው ግለሰብ ላይ የ50 ዓመት እስራት ፈርዶበታል። ውሳኔው በዘውዳዊው ሕግ ከፍተኛው ቅጣት ነው ተብሏል።
የሠላሳ ዓመቱ ሞንግኮል ቲራኮት ከሦስት ዓመታት በፊት በፌስቡክ ላይ ባሰራጫቸው ጽሑፎች መጀመሪያ ላይ የ28 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር።
የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሐሙስ ዕለት በዋለው ችሎት ተጨማሪ 22 ዓመታትን ጨምሮበታል።
በዘውዳዊው ሕግ መሠረት ማንኛው ስለአገሪቱ ንጉሣዊ ሥርዓት የሚሰጥ አሉታዊ አስተያየት በወንጀል ያስጠይቃል።
ከ10 ዓመታት በኋላ ባለፈው ዓመት በታይላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቪል መንግሥት በምርጫ ቢያሸንፍም ከፍተኛ ትችት የሚቀርብበት ሕግ አሁንም በሥራ ላይ ይገኛል።
ሐሙስ ዕለት በዋለው ችሎት ተከሳሹ ለሂደቱ ባሳየው ተባባሪነት ምክንያት ቅጣት በአንድ ሦስተኛ መቀነሳቸውን ዳኛው ገልጸዋል።
መኖሪያውን በቺያንግ ራይ ግዛት በማድረግ በበይነ መረብ ልብስ በመሸጥ የሚተዳደረው ቲራኮት ከባድ ቅጣት ለምን እንደተላለፈበት በዝርዝር አልተገለጸም።
ዳኛው በፌስቡክ ላይ የተሰጡ በርካታ አስተያየቶችን ጠቅሰዋል። የታይላንድ ፍርድ ቤቶች በግለሰቦች ለሚሰጡ እያንዳንዳቸው አሉታዊ አስተያየቶች ተጨማሪ ቅጣት ያስተላልፋሉ።
እአአ በ2019 ንጉሥ ቫጂራሎንግኮርን ወደ ዙፋኑ እንደመጡ ይህ ሕግ ለአጭር ጊዜ ታግዶ ነበር።
ከሦስት ዓመታት በፊት ታይቶ የማይታውቅ የተባለለትን እና በተማሪዎች የተመራ ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ሕጉ እንደገና በሰፊው ጥቅም ላይ መዋሉን ቀጥሏል። ተቃውሞው በንጉሣዊው ሥርዓት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረበ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ ስለንጉሣዊው ሥርዓት ሕዝባዊ ውይይት የጠራው የማኅበረሰብ አንቂው እና የሕግ ባለሙያው አርኖን ናምፓ የእስር ጊዜም በአራት ዓመት ከፍ ተደርጓል።