የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የብልጽግና ባለሥልጣናት የሚያካሄዱትን ወታደራዊ ዛቻ ቀጥለዋል ሲሉ ወነጀሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የብልጽግና ባለሥልጣናት በኤርትራ ላይ የሚያካሄዱት ግድየለሽነት የተሞላበት ወታደራዊ ዛቻ ቀጥለውበታል ሲሉ ከሰሱ።

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል፣ ረቡዕ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም. በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ላይ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት እና ''ተሳዳቢዎቻቸው'' በኤርትራ ላይ "በዘፈቀደ" የሚያካሂዱትን "ወታደራዊ ዛቻ" ዳግም ቀጥለውበታል ብለዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ በተላለፈው ውይይታቸው ላይ የቀይ ባሕርን ጉዳይ አንስተው የተፈጸመው ስህተት በቅርቡ ይታረማል ካሉ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪያቸው ጋር በነበራቸው በዚህ ውይይት ላይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን መጠናቀቅ አስመልክቶ ሲናገሩ የሺህ ዓመት የአባይ ታሪክ እንደተቀየረው ሁሉ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት ሁኔታም "ነገ ይታረማል፤ ብዙ ከባድ አይደለም" ብለዋል።

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ልጥፋቸው ላይ፣ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት የኤርትራን ጥንታዊ፣ የመካከለኛው ዘመን እና ዘመናዊ ታሪክ ያዛባሉ በማለት ወቅሰዋል።

የአሁኑ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት ንግግር ከኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ ጋር እንደሚያያዝ የጠቆሙት የማነ፣ ሕዝበ ውሳኔው ኤርትራን በወረራ የያዘችው አገር በቅድሚያ ፍላጎቷ ሊጠየቅ ወይም ሕዝበ ውሳኔውን እንድትቀበል በቅድመ ሁኔታነት ሊቀርብ የሚችልበት ሁኔታ እንዳልነበረ እና ሊኖርም እንደማይችል ገልጸዋል።

የማነ ይህን ያሉት፣ በቅርቡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ፣ ''ኢትጵያ የባሕር በር የምትጠይቅበት አራት አሳማኝ ምክንያቶች አላት'' በማለት ከዘረዘሯቸው ነጥቦች መካከል አንዱ አሰብ በወቅቱ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ተላልፎ መሰጠቱን ነው።

ኤርትራ ነጻነቷን ስታገኝ የአሰብ ወደብ ወደ ኤርትራ የሄደበትን መንገድ በማንሳት ያብራሩት ጄነራሉ፣ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት በመሆኑ "የባሕር በርን ያክል ለመስጠት ሕጋዊ ውክልና" አልነበረውም ብለው መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

"የሽግግር መንግሥት፤ በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት የባሕር በር አሳልፎ የመስጠት ማንዴት [ውክልና] የለውም።"

ኢትዮጵያ ከ30 ዓመት በፊት ኤርትራ ነጻ መውጣቷን ተከትሎ የባሕር በር የሌላት አገር በመሆኗ ከዚያ ጊዜ በኋላ ለገቢ እና ለወጪ ንግዷ የጂቡቲን ወደብ በመጠቀም ላይ ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የኅልውና ጉዳይ ነው ማለታቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተካረረ መጥቷል።

ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የባሕር በር በሰላማዊ እና በገበያ መርኅ ለማግኘት እንደምትፈልግ ቢጠቅሱም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግን "በጠብ አጫሪነት" ወንጅለዋል።

"ሉዓላዊ የባሕር በር" ማግኘት የሚለው ትኩረት መሳቢያ ገጽታዎች አሉት ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ከዚህ "ግድየለሽ ጀብደኝነት ጀርባ ሌሎች ኃይሎች አሉ" ብለው ነበር።

የማስታወቅያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ልጥፋቸው ላይ ኤርትራ እአአ ከ1940 ጀምሮ ነጻነቷን ለማግኘት መታገሏን በማንሳት ይህም በዓለም አቀፍ ሕግ ዕውቅና የተሰጠው የማይገረሰስ፣ ብሔራዊ እና ፖለቲካዊ መብት መሆኑን ጽፈዋል።

"ይህ በማንም ውድቅ ሊደረግ ወይም የማንም ሌላ አገር ወይም ዓለም አቀፍ አካል ይሁንታ የማያስፈልገው ነው።"

በማስከተል ደግሞ እአአ በ1993 የተካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ በማንሳት፣ ኤርትራን በወረራ የያዘችው አገር በቅድሚያ ፍላጎቷ ሊጠየቅበት ወይም ሕዝበ ውሳኔውን እንድትቀበል በቅድመ ሁኔታነት ሊቀርብ የሚችልበት ሁኔታ እንዳልነበረና ሊኖርም እንደማይችል ገልጸዋል።

በስተመጨረሻም የኤርትራ የመጨረሻ ምላሽ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እንዳሉት "በቤታችሁ ተሰብሰቡ" የሚል መሆኑን ተናግረዋል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረው የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ተሻሽሎ የነበረ ሲሆን፣ የኤርትራ ወታደሮች ለሁለት ዓመት በተካሄደው የትግራይ ጦርነት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፈው መዋጋታቸው ይታወሳል።

ነገር ግን በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም የአገራቱ ግንኙነት ተቀዛቅዟል።

ከዚህ በኋላም ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ያላትን ፍላጎት በይፋ መግለጿን ተከትሎ ሁለቱ አገራት አንዳቸው ሌላኛቸውን መወንጀል ጀምረዋል።

በሁለቱም ወገን የጦርነት ዝግጅት እንዳለ የተለያዩ ዘገባዎች እያመለከቱ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸው ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላት አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል።