በጋዛ ተኩስ አቁም ለማድረግ የሚካሄደው ንግግር ሊፈርስ ቋፍ ላይ መሆኑን የፍልስጤም ባለስልጣናት ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

እስራኤል እና ሀማስ በጋዛ አዲስ ተኩስ ማቆም ተግባራዊ እንዲሆን እና ታጋቾች እንዲለቀቁ በኳታር እየደረጉ ያሉት ንግግር ሊፈርስ አፋፍ ላይ መሆኑን የድርድሩ ዝርዝሮች የሚያውቁ የፍልስጤም ባለስልጣናት ተናገሩ።

አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን ጉብኝት ባደረጉት ጉዞ እስራኤል "ጊዜ ገዝታለች" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስራኤል በዋና ዋና አከራካሪ ነጥቦች ላይ ውሳኔ ለመስጠት እውነተኛ ስልጣን የሌለውን ልዑካን ወደ ዶሃ በመላክ ሆን ብላ ሂደቱ እንዲቆም አድርጋለች ሲሉም ከስሰዋል።

ከእነዚህ የንግግር ነጥቦች መካከል የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲሰራጭ ማድረግን ይገኙበታል።

ኔታኒያሁ ሐሙስ ዕለት ከአሜሪካ ከመመለሳቸው በፊት "በጥቂት ቀናት ውስጥ" ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስፋ እንዳላቸው በመግለጽ፤ ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል አዎንታዊ አመለካከት መያዛቸውን አመልክተው ነበር።

ለንግግር የቀረበው ስምምነት፤ ለ60 ቀናት በሚደረገው የተኩስ አቁም ጊዜ ውስጥ ሀማስ አሁንም ከያዛቸው 20 በህይወት ያሉ ታጋቾች መካከል ግማሾቹን እንዲሁም ህይወታቸው ካለፈው እስረኞች መካከል ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን እንዲለቅቅ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረው ነበር።

ካለፈው ሳምንት እሁድ ጀምሮ የእስራኤል እና የሀማስ ተደራዳሪዎች በዶሃ በተለያዩ ህንጻዎች ውስጥ ተቀምጠው ስምንት ቀጥተኛ ያልሆኑ "የቅርበት" ንግግሮችን አድርገዋል።

ንግግሮቹ የተመቻቹት በኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱል ራህማን አል ታኒ እና በግብፅ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት ሲሆን የአሜሪካው ልዑክ ብሬት ማክጉርክም በድርድሩ ላይ ተገኝተዋል።

አስታራቂዎቹ በሀማስ ልዑካን እና ወታደራዊ፣ የደህንነትና የፖለቲካ ባለሥልጣናትን ባካተተው የእስራኤል ልዑካን መካከል በደርዘን የሚቆጠሩ የቃል እና የጽሁፍ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

ነገር ግን ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው የፍልስጤም ባለስልጣናት፤ ሁለቱ ወገኖች በበርካታ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ እጅጉን የተከፋፈሉ በመሆናቸው የተነሳ ድርድሩ ሊፈርስ እንደተቃረበ አርብ ምሽት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመጨረሻዎቹ ንግግሮች ጋዛ የሰብአዊ እርዳታ የሚደርስበት አሰራር እና የእስራኤል ጦር በምን ያህል ደረጃ ለቅቆ ይወጣል በሚሉት ሁለቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሀማስ፤ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ መግባት አለበት እና መሰራጨት ያለበት በተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እና በዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በኩል ነው በሚለው አቋሙ ጸንቷል።

እስራኤል በበኩሏ፤ የእርዳታ ስርጭቱ 'ጋዛ ሂውማንተሪያን ፋውንዴሽን' (GHF) በተባለው በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፍፈው አወዛጋቢ አሰራር በኩል እንዲካሄድ ግፊት እያደረገች ነው።

በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉ አደራዳሪዎች እንደሚገልጹት፤ በገዳዩ ላይ ያለውን ልዩነት ማጥበብን በተመለከተ ውስን ውጤት ታይቷል። ነገር ግን መደበኛ ስምምነት ላይ አልተደረሰም።

ሁለተኛው ዋነኛ አከራካሪ ጉዳይ፤ እስራኤል በምን ያህል መጠን ለቅቃ ትውጣ የሚለውን የሚመለከት ነው።

በአምስተኛው ዙር ንግግር ወቅት፤ የእስራኤል ተደራዳሪዎች እስራኤል ጋዛ ውስጥ ከ1 እስከ 1.5 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የተገደበ "መከላከያ ቀጣና" (buffer zone) ይዛ እንደምትቆይ የሚገልጽ የጽሁፍ መልዕክት ለአደራዳሪዎች እንደሰጡ ተዘግቧል።

ቢያንስ ሁለት ዙር ውይይቶች ላይ የተገኙ አንድ የፍልስጤም ባለስልጣን፤ ሀማስ ይህንን ሃሳብ ለስምምነት መነሻ ነጥብ አድርጎ እንደተመለከተው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ሀማስ፤ እስራኤል ለቅቃ የምትወጣበትን ዞን የሚያሳይ ካርታ እንዲቀርብለት ከጠየቀ በኋላ የተሰጠው ሰነድ፤ ጦሩ እጅጉን ወደ ውስጥ ገብቶ እንደሚሰፍር የሚያሳይ እና አስቀድሞ ከተላለፈው መልዕክት የሚቃረን እንደሆነ ተነግሯል።

የቀረበው ካርታ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ ሶስት ኪሎ ሜትር ጥልቀት ያላቸው መከላከያ ዞኖችን እንደሚኖሩ የሚያመለክት እና በግዛቱ ሰፊ ክፍል ውስጥ እስራኤል እንደምትኖር የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።

የቀረበው እቅድ፤ ደቡባዊውን የራፋህ ከተማ ሙሉ በሙሉ፣ ከኻን ዩኒስ በስተ ምስራቅ የሚገኘውን የኩዛ መንደር 85 በመቶ፣ ሰሜናዊዎቹን ቤት ላሂያ እና ቤት ሐኖን ከተሞች ሰፊ ክፍሎች እንዲሁም በጋዛ ከተማ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኙትን እንደ ቱፋህ፣ ሸጃያ እና ዘይቱን ያሉ ሰፈሮች በሙሉ ይሸፍናል።

የሀማስ ባለስልጣናት የቀረበውን ካርታ፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን መተማመን የበለጠ እንዲቀንስ የሚያደርግ በእስራኤል በክፉ ልቦና የተፈጸመ ተግባር እንደሆነ አድርገው ቆጥረውታል።

የፍልስጤም ባለስልጣናት፤ የእስራኤል የልዑካን ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትያናሁ በቅርቡ በዋሽንግተን ላደረጉት ጉብኝት አዎንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ ለመፍጠር ሲሉ ሆን ብለው ንግግሩ እንዲጓተት አድርገዋል ሲሉ ይከስሳሉ።

አንድ ከፍተኛ የፍልስጤም ተደራዳሪ "ንግግሮቹን በጭራሽ በቁም ነገር አይመለከቷቸውም ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ንግግሮቹን ጊዜ ለመግዛት እና ውጤት እየተገኘ እንደሆነ በማስመሰል የተሳሳተ ምስል ለማቅረብ ተጠቅመውባቸዋል" ሲሉም አክለዋል።

በተጨማሪም ባለስልጣኑ እስራኤል በሰብአዊ እቅድ ሽፋን የረጅም ጊዜ በግዳጅ ማፈናቀል ስትራቴጂን እየተከተለች ነው ብለዋል።

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ፍልስጤማውያንን ራፋህ ውስጥ ወደሚገኝ "ሰብአዊ ከተማ" ለማዛወር ያቀዱት፤ የጋዛ ነዋሪዎችን በቋሚነት ለማፈናቀል የሚደረገው ሰፊ ጥረት አካል እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ፤ "ሰላማዊ ዜጎችን በግብፅ ድንበር አቅራቢያ የማሰባሰብ ዓላማ፤ በራፋ ወደ ግብጽ በሚሻገረው ወይም በባህር በሚያቋርጠው መስመር እንዲባረሩ መንገድ መጥረግ ነው" ብለዋል።

ሰኞ ዕለት ካትዝ ለእስራኤላዊያን ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ሰራዊቱ 600,000 ፍልስጤማውያንን የሚያስተናግድ አዲስ ካምፕ በራፋህ እንዲያዘጋጅ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል። ይህ ቁጥር ግን በኋላ ላይ ወደ 2.1 ሚሊዮን ከፍ ተደርጓል።

በእቅዱ መሰረት፤ ፍልስጤማውያን ከመግባታቸው በፊት በእስራኤላዊ ኃይሎች የደህንነት ምርመራ የሚደረግባቸው ሲሆን መውጣትም አይፈቀድላቸውም።

በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተቺዎች ሃሳቡን አውግዘዋል፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ምሁራን እና የህግ ባለሙያዎችም እቅዱን "የማጎሪያ ካምፕ" ንድፍ ሲሉ ጠርተውታል።

ውይይቱ አሳሳቢ መስቀለኛ መንገድ ላይ ባለበት በዚህ ጊዜ፤ በፍልስጤም በኩል ያሉ አካላት አሜሪካን የበለጠ ጠንከር ያለ ጣልቃ ገብነት እንድታደርግ እና እስራኤል ትርጉም ያለው ስምምነት ላይ እንድትደርስ ግፊት እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ አይነቱ ጣልቃ ገብነት የማይደረግ ከሆነ የዶሃው ድርድር ሙሉ በሙሉ ሊፈርስ እንደሚችል አደራዳሪዎች አስጠንቅቀዋል።

እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ለመፍጠር እና ጋዛ ውስጥ ሰፊ ሰብዓዊ አደጋን ለማስቀረት በቀጣናው የሚደረገውን ጥረት የበለጠ ያወሳስበዋል።

በዶሃ የሚገኙ ዲፕሎማቶች አሁንም ቢሆን ለስምምነት የሚያበቃ ጠባብ መስኮት እንዳለ ይናገራሉ፤ ግን ንግግሩ ቋፍ ላይ ነው።

አንድ የክልሉ ባለስልጣን "ይህ ሂደት በገመድ ላይ ተንጠልጥሎ ነው ያለው" ብለዋል። "የሆነ ነገር በከፍተኛ ሁኔታ እና በፍጥነት ካልተለወጠ በስተቀር ወደ መክሸፍ እየሄድን ሊሆን ይችላል" ብለዋል።