'በቁሙ ሞቷል' በሐማስ እገታ የሚገኘው ኢቪያታር ዴቪድ ወንድም

በጋዛ ሰርጥ በሐማስ ተይዞ የሚገኝ እስራኤላዊ ታጋች በረሃብ ተዳክሞ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምሥል በሐማስ መለቀቁ "አዲስ የጭካኔ መንገድ" ሲል ወንድሙ ለቢቢሲ ተናገረ።
ሐማስ የ24 ዓመቱን ኢቪያታር ዴቪድ አሁናዊ ሁኔታን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ቅዳሜ ዕለት የለቀቀ ሲሆን፤ ከእስራኤል እና ምዕራባውያን መሪዎች ጠንካራ ውግዘት ገጥሞታል።
የዴቪድ ወንድም ኢላይ "ነፍስ ያለው አፅም ነው። በየትኛው ቅፅበት ሕይወቱ ሊያልፍ እስከሚችል ድረስ አስርበውታል። እናም በእጅጉ እየተሰቃየ ነው። መናገር እናኳ አይችልም፤ መንቀሳቀስ አይችል" ሲል ተናግሯል።
በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ኢቪያታር "ለቀናት ምግብ አልተመገብኩም። . . . ውሃ እንኳ አልጠጣሁም" ሲል ተደምጧል።
በምሥሉ መሬት ሲቆፍር የሚታይም ሲሆን፣ መቀበሪያው እንደሆነም ይናገራል።
የታጋች ቤተሰቦች ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሐማስ የታገቱ ሰዎችን ማስለቀቁ ቅድሚያ እንዲሰጡ እየወተወቱ ባለበትበዚህ ሰዓት፤ የወታደራዊ ዘመቻውን ለማስፋፋት መወጠናቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
የኢቪያታር ዴቪድ ምሥል የተለቀቀው የፍልስጤም ኢስላሚክ ጅሃድ የተባለው ቡድን ሮም ብራስላቭስኪ የተባለ የሌላ ታጋች ምሥል ከለቀቀ በኋላ ነው።
መስከረም መጨረሻ 2016 ዓ.ም. ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት ሲከፍት ሁለቱ እስራኤላውያን ከኖቫ የሙዚቃ ፌስቲቫል ታግተው የተወሰዱ ናቸው።
እነዚህ እስራኤላውያን በጋዛ ታግተው ከሚገኙ 50 ታጋቾች መካከል ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ 20 የሚሆኑት እስካሁን በሕይወት አሉ ተብሎ ይታመናል።
ኢላይ ዴቪድ አባቱ የታጋች ወንድሙን ድምፅ መለየት እንደተሳናቸው እና መተኛት እንደማይችሉ ተናግሯል።
እናቱ ደግሞ ቀኑን ሙሉ ማልቀሳቸውን ተናግሯል።
"ወንድሜ አፅሙ ብቻ ቀርቶ ማየታችን፤ አዲስ ዓይነት ጭካኔ መሆኑን ነው የተረዳነው" ያለው ዴቪድ፤ "ይህ የመጨረሻ ውድቀት ነው" ብሏል።
የዓለም መሪዎች ወንድሙን እና ሌሎች ታጋቾችን "በጭካኔ ከተሞሉት የሐማስ እጆች" እንዲያስለቅቋቸው እና እንዲያገናኟቸው ጥሪ አቅርቧል።
"መልዕክታችንን ለማድረስ ትኩረት ማድረግ አለብን። ይህም መልዕክት ኢቪያታር እየሞተ ነው፤ መድኃኒት ልንሰጠት ያስፈልጋል፤ ደኅና ምግብ ልንሰጠው እና እርዳታ የማንሰጠው ከሆነ ይሞታል" ሲል ወትውቷል።
የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ እስረኞችን ሆን ብሎ ማስራቡን የካደ ሲሆን፤ ታጋቾች ወታደሮች እና የጋዛ ሕዝቦች የሚመገቡት ነው የሚመገቡት ብሏል።
የታጋቾች ተንቀሳቃሽ ምሥል ይፋ ከሆነ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ከታጋች ቤተሰቦች ጋር ተነጋግረዋል።
ታጋቾችን የማስመለስ ጥረት "ያለማቋጥ እና ደከመን ሳንል እንቀጥላለን" ብለዋል።
ይሁን እንጂ አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን ኔታኒያሁ ታጋቾችን ለማስቀቅ እየሠሩ ያሉት መንገድ "ሐማስን በጦር በማሸነፍ" ነው ብለዋል።
በጋዛ ሊከሰት የሚችል አዲስ ዘመቻ ፍልስጤማውያን በረሃብ እና ምግብ እጥረት እየሞቱ ነው የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚፈልጉትን የእስራኤል አጋሮችን የበለጠ ሊያበሳጭ ይችላል።
የታጋች ቤተሰቦችን በዋነናነት የሚደግፍ ቡድን የአዲስ ወታደራዊ ዘመቻን በመቃወም "ኔታኒያሁ እስራኤልን እና ታጋቾችን ወደ ጥፋት እየወሰዱ ነው" ብሏል።
ይህ ሀሳብ 600 በሚሆኑ ጡረተኛ የእስራኤል የደኅንነት ሹማምንት ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በላኩት ደብዳቤ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ትራምፕ እስራኤል በጋዛ ያለውን ጦርነት በአፋጣኝ እንድታቆም ጫና እንዲያሳድሩ ጠይቀዋል።
ቡድኑ የቀድሞ የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ አዛዥ ታሚር ፓርዶ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚነስትር ኢሁድ ባራክ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን ሞሼ ኣላንን ያካትታል።
የሐማስን የመስከረም 26/2015 ዓ.ም. መጨረሻ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።
በሐማስ ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
የእስራኤልን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ ደግሞ 60 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር አሳውቋል።















