ጆ ባይደን መካከለኛው ምሥራቅን ሊጎበኙ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጆ ባይደን ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በማቅናት እስራኤል፣ የፍልስጤም ግዛቶችን እና ሳዑዲ አረቢያን ሊጎበኙ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በሚቀጥለው ወር የሚያደርጉት ጉብኝት ለአራት ቀናት የሚቆይ ነው።
ባይደን ወደ መንበር ሥልጣኑ ከመጡ ካለፈው ዓመት በኋላ የአሜሪካ እና የአጋሮቿ ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ቆይቷል።
ዋይት ሐውስ የእስራኤልን የሰፈራ ፕሮግራም ተችቷል። ፍልስጤማዊያን በበኩላቸው ከፍተኛ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየጠየቁ ነው። ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላት ግንኙነት ደግሞ በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ መገደል ምክንያት ተቀዛቅዟል።
ባይደን እአአ በ2019 ለፕሬዝዳንትነት የምርጫ ዘመቻ ሲያደርጉ ከጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ ሳዑዲ አረቢያን “እንደማያቀርቡ” ቃል ገብተው ነበር።
የሳዑዲ ዝርያ ያለው ኻሾግጂ ለዋሽንግተን ፖስት በመጻፍ ይታወቅ ነበር። ጋዜጠኛው በ2018 ቱርክ ውስጥ ወደሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ እንዲገባ በማድረግ መገደሉ ይታወቃል።
የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋዜጠኛው እንዲያዝ ወይም እንዲገደል ፈቃድ ሰጥተዋል ሲሉ የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ከድምዳሜ ደርሰዋል።
ልዑሉ በግድያው ምንም ሚና አልነበረኝም ሲሉ ያስተባበሉ ሲሆን ሳዑዲ “ሥርዓት አልበኛ” የደኅንነት አባላት የፈጸሙት ነው ብላለች።
ልዑል ሞሐመድ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው። ባይደን ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ዋይት ሐውስ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን ግንኙነት “በድጋሚ እንደሚያጤኑት” ገልጿል።
ባይደን አሁን ካለው የነዳጅ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ሳዑዲን ማራቅ ተገቢ አለመሆኑ ሳያሳምናቸው አልቀረም።
ሁለቱ መሪዎች በኃይል አቀርቦት ዙሪያ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፕሬዝዳንቱ ጉብኝታቸው ከነዳጅ ይልቅ ከደኅንነት ጋር የተያያዘ መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል።
ይህ ግንኙነት በባይደን እና በልዑል ሞሐመድ መካከል ፊት ለፊት የሚደረግ መጀመሪያው ውይይት ይሆናል።
“ልዑሉ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት እና የሰብዓዊ ድጋፍ ጥሰት እንዲፈጽሙ የሚያበረታታቸው ነው” ሲሉ 13 የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ጉብኝቱን ኮንነዋል።
“[የባይደን] አስተዳደር የልዑሉን ገጽታ ከመገንባቱ በፊት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ መሥራት ይገባዋል” ብለዋል።
አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሰብዓዊ መብት እና ሳዑዲ የምትደግፋቸው የመንግሥት ኃይሎች በኢራን ከሚደገፉት የሁቲ ኃይሎች ጋር በየመን የሚያደርጉት ጦርነት በአጀንዳነት ተይዘዋል ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባይደን ከእስራኤል በቀጥታ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመብረርም የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።
ሳዑዲ እና ሪያድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላቸው ሲሆን በሁለቱ አገራት መካከልም በረራ ብዙም አይፈቀድም። ልዑሉ በቅርቡ ነው የእስራኤል የመንገደኘች አውረፕላኖች በአየር ክልላቸው በኩል እንዲበሩ የፈቀዱት።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት እያሻሻለች ነው። በሳዑዲ በኩል ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ያለው ጉዳይ መፈታት እንደሚገባውም ልዑሉ አስታውቀዋል።
አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጉዞው "እስራኤል ቀጣናው ጋር የምታደርገው መቀራረብ ላይ ያተኩራል" ብለዋል።
ባይደን በጉብኝታቸው ከእስራኤል ከጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ጋር ይወያያሉ። ቤኔት በዌስት ባንክ የእስራኤል የሰፈራ ግንባታ እንዲከናወን የሚደግፉ ናቸው። የባይደን አስተዳደር ደግሞ ይህንን "በጽኑ ይቃወማል።"
በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ሰፈራ መንደሮቹ ሕገ-ወጥ እንደሆኑ ቢገለጽም እስራኤል አትቀበለውም።
ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም ከፍልስጤም አቻቸው ማህሙድ አባስ ጋር በዌስት ባንክ ይገናኛሉ። የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደሚሉት ባይደን ለእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት “የሁለት-አገራት መፍትሄ ይገባል የሚለውን የዕድሜ ልክ አስተሳሰባቸውን እንደሚያረጋግጡ” ይጠበቃል።
ይህም ከእስራኤል ጎን ለጎን የፍልስጤም መንግሥት መፍጠርን የሚደግፍ ነው። ቤኔት ይህ ፈጽሞ የማይሞከር ነገር ነው ብለዋል።
የጉብኝቱ ይፋ የተደረገው አሜሪካ ከፍልስጤማውያን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካሻሻለች ከቀናት በኋላ ነው። ይህም የትራምፕ አስተዳደር በእየሩሳሌም የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ በ2018 ስለመዘጋቱ የተሰጠ ምላሽ ተደርጎ ይወሰዳል።
ፍልስጤማውያን እንደ ኤምባሲ የሚቆጥሩት ቆንስላ ድጋሚ ባለመክፈቱ ቅር ተሰኝተዋል። ትራምፕ መላው እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ አድርገው በመቀበላቸው ፍልስጤማውያንን ቆሽት ያሳረረ ነው። ይህ ሁኔታም በባይደን አስተዳደር ላይም ቆይቷል።
ፍልስጤማውያን ምሥራቅ እየሩሳሌምን የወደፊቷ ነጻ አገራቸው ዋና ከተማ አድርገው ይመለከቷታል። እስራኤል በ1967 በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የተቆጣጠረችውን ምሥራቁን ክፍል ጨምሮ መላውን እየሩሳሌም እንደዋና ከተማዋ ትቆጥራለች።












