በጦርነቱ ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች በመቀለ ሲገናኙ የነበረው ስሜት

ታትሟል

ትናንት ታህሳስ 19፣ 2015 ዓ.ም ለመቀለ ነዋሪዎች የተለየች ነበረች።

ለአስራ ስምንት ወራት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል።

ደም አፋሳሹን ጦርነት ተከትሎ ትራንስፖርትም ሆነ መሰረታዊ አገልግሎቶች በተቆረጡባት ትግራይ ክልል በረራ እንደገና ተጀምሯል።

ትናንት ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ እኩለ ቀን ላይ የተነሳው አውሮፕላን መቀለ ካረፈ በኋላም በተለያዩ ስሜቶች የተዋጡ መንገደኞች ታይተዋል።

መንገደኞችም በመቀለ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ሲደርሱም መሬቱን ሲሳለሙ፣ በርካቶች ሲላቀሱ፣ ሲተቃቀፉም ታይተዋል።

ለአንድ ዓመት ተኩል ያላይዋቸውን ቤተሰቦች፣ ወዳጆች ዘመዶችም ጋር አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ሲላቀሱ ታይተዋል።

ወደ አምስት መቶ ሺህ ህዝብ የሚጠጋ ህዝብ ያላት የመቀለ ከተማ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈውና ሚሊዮኖችን ቤት አልባ አድርጎ ባፈናቀለው ለሁለት ዓመታት በዘለቀው አሰቃቂ ጦርነት ከዓለም ተነጣጥላ ነበር።

የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሃት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ተከትሎ በረራ መልሶ እንዲጀምር መንገድ ከፍቷል።

በመቀለ አሉላ አባነጋ ማሪፊያ መንገደኞች ተንበርክከው እንዲሁም አስፋልቱን ሲሳለሙ የሚያሳዩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች የትግራይ ቴሌቪዥን አሳይቷል።

የትግራይ መንገደኞችም በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ማረፊያ ሲደርሱ በርካታ ስሜታዊ ትዕይንቶች ተስተናግደዋል።

የስልክ አገልግሎት በመቋረጡና ከ18 ወራት በላይ ከቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው የተቆራረጡ የትግራይ ተወላጆች በህይወት ይኑሩ አይኑሩ አያውቁም። በዚህ በረራ ተሳፍረው እንደሚመጡ የማያውቁ ቤተሰቦችም መቀለ ሲደርሱና በየቤታቸው ሲገቡ የነበረውን ድንጋጤ፣ ደስታ፣ ለቅሶ የትግራይ ቴሌቪዥን አሳይቷል።

ለፈተና እየዘጋጀች የነበረች ልጇ ጋር አብራ ለመሆን ወደ አዲስ አበባ የመጣችው የ47 አመቷ ካህሳይ ኃይሉ ትራንስፖርት መቋረጡን ተከትሎ ከቤተሰቦቿ ጋር ሳትገናኝም ለረዥም ጊዜያት ተቆራርጣ ነበር።

“ከምወዳቸው ባለቤቴና ልጄ ተለይቼ ኑሮዬን በአዲስ አበባ አድርጌ ነበር” ስትልም ካህሳይ ወደ መቀለ ጉዞዋን ለማድረግ በቦሌ አየር ማረፊያ እየተጠባበቀች በነበረበችበት ወቅት ለሮይተርስ ተናግራለች።

አክላም “የአየር በረራዎች እንደገና መጀመሩን ዜና በሰማሁ ጊዜ መሬት ላይ ወድቄ አለቀስኩ” ብላለች።

ሌላኛው የ67 ዓመቷ ንግሥት ኃይለማርያም ነፍሰጡር ልጃቸውን ለማዋለድና ለማረስ በ2020 አዲስአበባ መግባታቸውን ይናገራሉ።

“ነፍሰጡር ልጄን አዋልጄ ለማረስ ነበር የመጣሁት። በአዲስ አበባ ሁለት ሳምንት ብቻ ለመቆየት ነበር ዕቅዴ። ከዚያም ሁሉ ነገር ተዘጋ፤ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይም ሆኖታል። ሰላም እየሰፈነ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ። በመጨረሻም ወደ ቤቴ ልሄድ ነው” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈውና በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ የማይነገር ሰቆቃ ያደረሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በፌደራሉ መንግሥትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

የሰላም ስምምነቱ ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መሠረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።