ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ በቪላ ከተሸነፈ ቴን ሃግ ይባረራሉ? የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ግምት
ማንቸስተር ዩናይትድ እሑድ ዕለት ከአስቶን ቪላ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል። ጨዋታው ጫና ውስጥ ለገቡት አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ የመጨረሻቸው ይሆን?
“የትኛውን ዩናይትድን እንመለከት ይሆን?” ሲል የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ይጠይቃል። “ከቶተንሃም ጋር የነበረውን ዓይነት አጨዋወት ከደገሙት ሽንፈት አይቀሬ ነው” ይላል።
“ቴን ሃግ ውጤት ሲፈልጉ ቡድኑ ውጤታማ መሆንን አሳይቷል። አሁንም ይህ የውጤት መሻሻል በአሰልጣኙ በኩል ይጠበቃል” ብሏል።
ሱተን የዚህን እና የሌሎችንም ጨዋታዎች ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።
ቅዳሜ
ክሪስታል ፓላስ ከ ሊቨርፑል
የአርን ስሎት ቡድን ከዓለም አቀፍ ውድድሮች በፊት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርበታል። ያሳካዋልም።
በጥሩ አቋም ላይ የማይገኘውን ፓላስን ያሸንፋሉ።
ፓላስ፣ ዎልቭስ፣ ሳውዝሃምፐተን፣ ሌስተር እና ኢፕስዊች ዘንድሮ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻሉ ቡድኖች ናቸው።
ኦሊቨር ግላስነር ቡድኑን ሲረከቡ ውጤታማ ቢሆኑም አሁን ግን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
ግምት፡ 1 – 2
ውጤት፡ 0 - 1
አርሰናል ከ ሳውዝአምፐተን
ከሳውዝአምፐተን በተቃራኒ አርሰናል አንድን ጨዋታ በምን አይነት መንገድ እንደሚያሸንፍ የሚያውቅ ቡድን ነው።
አሰልጣኝ ራስል ማርቲን ቡድናቸው በበርንመዝ መሸነፉን ተከትሎ ተጫዋቾችን በይፋ መተቸታቸው ጥሩ ስሜት አይኖረውም።
አሰልጣኙ ለአጨዋወታቸው ታማኝ ቢሆኑም አርሰናል ግን ርህራሄ የለሽ መሆኑን እያሳየ ነው።
የመድፈኞቹ የተከላካይ መስመር ጠንካራ ሲሆን ጎል ሳይቆጠርበት ጨዋታውን 3 ለምንም ያሸንፋል።
ግምት፡ 3 – 0
ውጤት፡ 3 - 1
ብሬንትፎርድ ከ ዎልቭስ
ዎልቭስ ጥሩ እየተጫወተ ቢሆንም በአንድ ነጥብ በደረጃው ግርጌ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።
የጋሪ ኦኒል ቡድን ውጤታማ የሚሆን ቢሆንም ብሬንትፎርድም ከሰሞኑ ጥሩ መንቀሳቀስ ጀምሯል።
ብሬንትፎርዶች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጎሎችን በማስቆጠራቸው ዎልቭሶች ለዚህ መዘጋጀት አለባቸው።
ሦስቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት ብሬንትፎርዶች በዚህ ጨዋታ ሦስቱን ነጠብ ያሳካሉ።
ግምት፡ 2 – 1
ውጤት፡ 5 - 3
ሌስተር ከ በርንመዝ
በርንመዝ ጥሩ ቡድን መሆኑን እያሳየ ይገኛል።
ኤቫንሊስን እና አንቶኒ ሴመንዮ በጥሩ አቋም ላይ ሲሆኑ በዚህ ጨዋታ ቡድኑ ሦስት ነጥብ የማሳካት ዕድል አለው።
ሌስተሩ አሰልጣኝ ስቲቭ ኩፐር ውጤት ማስመዝገብ ቢገባቸውም በዚህ ጨዋታ ግን ነጥብ አያገኙም።
ግምት፡ 1 – 2
ውጤት፡ 1 - 0
ማንቸስተር ሲቲ ከ ፉልሃም
ፉልሀም ወደ ኤቲሃድ ስታዲየም በመሄድ ምንም ነጥብ አያገኝም።
ማንቸስተር ሲቲዎች ባለፈው ሳምንት ከኒውካስል ጋር በነበራቸው ጨዋታ ጥሩ ባይሆኑም በዚህ ጨዋታ መሻሻል ይኖርባቸዋል።
ሚዛኑን የጠበቀ ቡድን ያለው ፉልሃም ከጨዋታው ምንም ውጤት ባያስመዘግብም፤ እንደባለፈው ዓመት 5 ለ 1 አይሸነፍም።
ዋናው ጥያቄ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ጎል ያስተናገዱት ሲቲዎች በዚህ ጨዋታስ ጎል ይቆጠርባቸው ይሆን የሚለው ነው።
ግምት፡ 3 – 0
ውጤት፡ 3 - 2
ዌትስ ሃም ከ ኢፕስዊች
ኢፕስዊች በጣም የተደራጀ ከመሆኑም በላይ በወቅታዊ አቋም ከዌስት ሃም የተሻሉ ናቸው።
ይህንንም ባለፈው ሳምንት ከአስቶን ቪላ ጋር አቻ በመውጣት አሳይተዋል። ብቸኛው ደካማ ጎናቸው እስካሁን አንድም ጨዋታ አለማሸነፋቸው ነው።
ዌስት ሃሞች ጥሩ ቡድን ቢኖራቸውም እስካሁን ሜዳ ላይ ማሳየት አልቻሉም። ይህ ጨዋታ ግን ውጤት ማግኘት ሚጀምሩበት ይሆናል።
አሰልጣኝ ዩለን ሎፔቲጉ ብቻ ሳይሆኑ ደጋፊውም ከዚህ ጨዋታ ውጤት ይጠብቃል።
ግምት፡ 2 – 0
ውጤት፡ 4 - 1
ኤቨርተን ከ ኒውካስል
ይህ ለመገመት ከባድ የሆነ ጨዋታ ነው።
ኒውካስል ባለፈው ሳምንት የውድድር ዓመቱን ምርጥ ብቃታቸውን ከማንቸስተር ሲቲ ጋር አሳይተዋል። የሚደግሙት ግን አይመስልም።
ኤቨርተኖች የመጀመሪያ ድላቸውን ከማስመዝገባቸውም በተጨማሪ ኢሊማን ንዲያዬ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል። ጃራድ ብራንትዌትም ከጉዳት ተመልሷል።
ምን አይነት ውጤት እንደሚኖር ለመገመት የሚያስቸግር ጨዋታ ነው።
ግምት፡ 1 – 1
ውጤት፡ 0 - 0
እሑድ
አስቶን ቪላ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
አስተን ቪላ የጉዳት ስጋት አለበት። ከባየር ሙኒክ ጋር በነበረው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ አማዱ ኦናና ተጎድቶ ሲወጣ ሊዮን ባይሊም ተቀይሮ ከገባ በኋላ ለመውጣት ተገዷል። ግብ ጠባቂው ኤሚ ማርቲኔዝም ስጋት አለበት።
በዚህ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ ከባድ ሽንፈት ካስተናገደ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ከኃላፊነታቸው ይነሳሉ።
ይህ ግን የሚሆን አይመስልም። ማንቸስተር ዩናይትድ ነጥብ ለማግኘት ትልቅ ፍላጎት አለው።
ዋናው ነገር አስቶን ቪላ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ድል በኋላ ለዚህ ጨዋታ ምን ያህል ዝግጁ ይሆናል የሚለው ነው።
ግምት፡ 1 – 1
ቼልሲ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ዘንድሮ የቼልሲ ውጤት ተገማች ቢሆንም የሚያስቆጥራቸውን ጎሎች መገመት ግን ከባድ ነው።
ኮል ፓልመር ድንቅ አቋም ላይ ይገኛል።
ለዓይን ማራኪ የሆነ ጨዋታ ከማሳየቱም በላይ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በሙሉ ጎል የሚያስቆጥር ተጫዋች እየመሰለ ነው።
የቼልሲ ተከላካይ አስተማማኝ ባለመሆኑ ፎረስት ጎል ማስቆጠር ቢችልም ድሉ የቼልሲ ይሆናል።
ግምት፡ 2 – 1