በሰሜን ወሎ በከባድ መሳሪያ በተፈፀመ ጥቃት ታዳጊዎችን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን እሁድ ሰኔ 22/2017 ዓ.ም. በተፈፀመ ተደጋጋሚ 'የሞርታር' ጥቃት ታዳጊዎችን ጨምሮ አራት ሰዎች ሲገደሉ ሰባት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች እና የአካባቢው አስተዳደር ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጥቃቱ የተፈፀመው በግዳን ወረዳ ዋና ከተማ ሙጃ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ40 አካባቢ ሲሆን፤ የአካባቢው አስተዳደር ጥቃቱን የፈፀሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች ናቸው ብሏል።

ጥቃቱ በመንግሥት የተጠራ 'ሕዝባዊ ሰልፍ' መዳረሻ እንደሆነ በታመነበት ኳስ ሜዳ እና በዙሪያው መድረሱን ሦስት ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል አያሌው አምስት የሞርተር ጥይት መወርወሩን ገልፀው፤ ጥቃቱ ሰልፉን ለማስተጓጎል ዒላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

ጥቃቱ ሲፈፀም ከከተማው ጫፍ ሰልፉ ወደ ሚጠናቀቅበት ኳስ ሜዳ እያመራ እንደነበር የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ይህን ተከትሎ ሰልፉ ባለበት እንዲቆም እና እንዲጠናቀቅ መደረጉን ተናግረዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ "ሁሉም ሰው በስጋት እየተሯሯጠ ነበር። ወደ ሐኪም ቤት የሚሄድ አለ፤ ቤተሰቡን የሚፈልግ አለ። ግርግር ነው የነበረው" ሲሉ ከጥቃቱ በኋላ ነበረውን ሁኔታ አመልክተዋል።

ሁለቱ የሞርታር ቅንቡላዎች የግለሰብ ቤቶች፣ ሁለቱ ሰልፉ ይካሄድበታል ተብሎ በታመኑ እና ሕዝባዊ ኩነቶች በሚካሄዱባቸው ስፍራዎች እንዲሁም አንዱ ከከተማው ወጣ ባለ ገጠራማ ስፍራ ማረፋቸውን አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

ጥቃቱ ሲፈፀም ኳስ ሜዳው አካባቢ ፀሐይ እየሞቁ እንደነበር የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ ሁለተኛው ቅንቡላ (የከባድ መሳሪያ ጥይት) ኳስ ሜዳው ውስጥ ማረፉን እና "ከባድ ፍንዳታ" መከሰቱን ገልፀዋል።

ወደ ኳስ ሜዳ በፍጥነት መድረሳቸውን የተናገሩት እማኙ ፍንዳታውን ተከትሎ "እሪታ፤ ኡኡታ" መከሰቱን ተናግረዋል።

"በጣም ከፍተኛ ድንጋጤ ነው የተከሰተው። ኳስ ሜዳ ውስጥ ብዙ ወጣቶች ነበሩ። ሕዝቡ ላይ መረበሽ ነበር። የማን ልጅ እንደሞተ ለማወቅ ሕዝቡ [እየተሯሯጠ] ነበር። . . .ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ጭንቀት እና ድንጋጤ ነበር" ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ሰልፍ ወጥተው እንደነበር እና የፍንዳታ ድምፅ ሰምተው ወደ ኳስ ሜዳ እንዳቀኑ የተናገሩ ሌላ የዓይን እማኝ ጉዳቱን "አስከፊ" ሲሉ ገልፀውታል።

የወረዳው አስተዳዳሪ ጥቃቱ ሰልፈኞቹ ሰልፉ ወደ ሚጠናቀቅበት ኳስ ሜዳ እየተጓዙ መሀል ከተማ ላይ እንደደረሱ መፈፀሙን ገልፀው "ማኅበረሰቡ ትንሽ ተደናገጠ። አረጋግተን፤ ሌላ ቦታ ላይ እንዲጠናቀቅ አድርገናል" ብለዋል።

አብዛኞቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ኳስ ሲጫወቱ የነበሩ ታዳጊዎች መሆናቸውን የተናገሩት እማኞቹ፤ ኳስ ሲጫወቱ የነበሩ ሁለት ታዳጊዎች "ሆዳቸው እና እግራቸው" ተመትቶ ሕይወታቸው እንዳለፈ ተናግረዋል።

"እኛ [ወደ ሕክምና] እስከምንወስዳቸው ሕይታቸው አልፏል" ሲሉ እማኝነታቸውን የሰጡት ነዋሪው፤ አንደኛው ታዳጊ ለሕክምና ወደ ወልዲያ እየተወሰደ እያለ መንገድ ላይ ሕይወቱ ማለፉን ጠቁመዋል።

በጥቃቱ የሞቱት "ከ13 እስከ 15 ዓመት [ይሆናሉ]፤ ከዚህ የሚበልጡ አይደሉም። ሕፃናት ናቸው" ሲሉ ሌላ እማኝ ስለ ሟቾቹ ማንነት ተናግረዋል።

ከከተማው ወጣ ባለ ስፍራ ደግሞ ወንድም እና እህት ናቸው የተባሉ ሁለት አንድ ቤተሰብ አባላት በጥቃቱ ሕይወት ሲያልፍ፤ የሟቾች አባት ደግሞ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች እና የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በዚህ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሰባት የሚሆኑ ሰዎች ቆስለው ለሕክምና ሙጃ ጤና ጣቢያ እንደተወሰዱም ገልፀዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል "አምስት ወንዶች፤ ሁለት ሴቶች በአጠቃላይ ሰባት ሰዎችን አቁስሏል። አንደኛው ብቻ ነው ትልቅ ሰው፤ ሌሎች ሕፃናት ናቸው" ብለዋል።

ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ቁስለኞች ወደ ወልዲያ ሆስፒታል ለሪፈራል ሕክምና መላካቸውንም አስተዳዳሪው አክለው ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው ጥቃቱን የፈፀሙት የፋኖ ኃይሎች እንደሆኑ የተናገሩ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃት እንደፈፀሙ አመልክተዋል።

አንድ ነዋሪ በበኩላቸው "ወደዚህ ሊተኩስ የሚችል ሌላ የታጠቀ አካል የለም። በዙሪያው ያሉት እነርሱ ናቸው። እንደዚህ ዓይነት መሳሪያ ከዚህ በፊት እንደተኮሱ የምናውቀው ነገር አለ" ሲሉ ጥቃቱን የፈፀሙት የፋኖ ኃይሎች ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

"ሕዝቡን የካደ" ሲሉ ጥቃቱን የገለፁት የሰሜን ወሎ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈለቀ ጌትነተ የጥቃቱ ዓላማ "ሕዝቡን ለመበተን ነው። ሕዝቡ የሚያመራው ወደ ኳስ ሜዳ ነበር። ሕዝቡን ለመበተን ታቅዶ የተሠራ ነው" ብለዋል።

ከግዳን ወረዳ ባለፈ በላስታ ወረዳም "ሰልፍ ለመበተን" ተመሳሳይ ጥቃት መፈፀሙን፤ ነገር ግን ሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን አቶ ፈለቀ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንድ ነዋሪም ጥቃቱ የተፈፀመው "ሰልፉን ለማስቆም" ታስቦ እንደሆነ እምነታቸውን ተናግረዋል።

የሟቾች የቀብር ሥነ ሥርዓት እሁድ እና በማግስቱ ሰኞ ሙጃ ማሪያም በተባለ ቤተ ክርስቲያን መፈፀሙን ነዋሪዎች ገልፀዋል።

"እስካሁኗ ቀን ድረስ ከተማዋ ላይ መረጋጋት አይታይም። በጣም ከፍተኛ ስጋት አለ። እዚያ አካባቢ [ኳስ ሜዳ አካባቢ] ዝር የሚል ወጣት አይገኝም" ሲሉ አንድ ነዋሪ ስጋቱን ገልፀዋል።።

"[ጥቃቱ] ጥሎት ያለፈው ጠባሳ በቀጣይስ ምን ሊፈጠር ይችላል? በሚል [ማኅበረሰቡ] ስጋት አለው። ከነበረው ሁኔታ አንፃር አሁን በዙሪያው ሰላም አለ፤ ተኩስ የለም" ሲሉ ሌላ ነዋሪ አሁናዊ ሁኔታው ተናግረዋል።

ቢቢሲ ጥቃቱን ፈፀሙ የተባሉትን የፋኖ ኃይሎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ግጭት እየተካሄደበት ባለው የአማራ ክልል እሁድ ሰኔ 22/2017 ዓ.ም. በተለያዩ አካባቢዎች መንግሥትን የሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፎች በተለያዩ አካባቢዎች ተካሂደዋል።

ሰልፎቹ በዋናነት በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን እና መንግሥት ሕግን እንዲያስከብር የሚጠይቁ መፈክሮችም ተሰምተዋል።