በነቀምቴ ከተማ በቡድን ከተደፈሩ ሁለት ታዳጊ ሴቶች ጋር በተያያዘ ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, ULLSTEIN BILD
በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ሁለት ታዳጊ ሴቶችን በቡድን በመድፈር፣ ወንጀሉ ሲፈጸም ቪድዮ በመቅረጽ እና በማህበራዊ ሚድያ በማጋራት የተጠረጠሩ ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።
በነቀምቴ ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ሸዋዬ ዲዳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አምስቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ወንጀሉ ሲፈጸም ቪድዮ ቀርጾ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ በማጋራት መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዱ ግለሰብ ግን የመድፈር ወንጀሉን በመፈጸም መጠርጠሩን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኮሚሽነር ሻሎ ገለታ ወንጀሉ የተፈጸመው ባለፈው መስከረም ወር ላይ መሆኑን ለቢቢሲ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ረቡዕ፣ ጥቅምት20/ 2017 ዓ.ም መሆኑን የገለጹት የሕግ ባለሙያዋ፣ ገመቹ ወይም ማሜ ተብሎ የሚታወቅ ተጠርጣሪ እየተፈለገ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።
ከወንጀሉ ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ስር የዋሉት ስድስቱ ግሰቦች ሐሙስ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ ታዳጊ ልጆች በቡድን ሲደፈሩ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምሥል ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ከተሠራጨ በኋላ በርካቶች ቁጣቸውን እየገለፁ ነው።
የነቀምቴ ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት መብራቴ ባጫ ከቀናት በፊት አራት ተጠርጣሪዎችን መለየታቸውን ተናግረው ነበር።
በወቅቱ “በቪድዮው ላይ የሚታዩ አራት ጥቃት አድራሾችን ለይተናል። የባጃጅ ሹፌሮች መሆናቸውንም ደርሰንበታል። አንዱ ባጃጁን ጥሎ የጠፋ ሲሆን የፀጥታ አካላት ክትትል አድርገው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተነጋግረናል” ነበር ያሉት
የቢሮ ኃላፊዋ መብራቴ ባጫ እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ተከታትሎ ጥቃት አድራሾችን ለፍትህ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፣ ሴቶች በነጻነት ወጥተው እንዲገቡ የሕግ የበላይነት መረጋገጡን እንከታተላለን ብለው ነበር።
አክለውም ይህ ዓይነት ከማኅበረሰቡ ሞራል ያፈነገጠ ተግባር እንዳይደገም ቢሯቸው የበኩሉን እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ይህ በታዳጊ ሕጻናቱ ላይ በደቦ የተፈጸመውን ወንጀል የሚያሳየው ቪዲዮ ላይ የጥቃቱ ሰለባዎች ገጽታ የሚታይ ሲሆን፣ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ፊት ግን ለመለየት በሚያስችል ሁኔታ አይታይም።
ድርጊቱ ቁጥቋጦ በሆነ ስፍራ ላይ ሲፈጸም የወንጀሉ ፈጻሚዎች እንዲሁም ቪዲዮውን የሚቀርጸው ሰው ሲነጋገሩ ይሰማል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮች ላይ በስፋት ሲዘዋወር የነበረው ይህ የወንጀል ድርጊት ቪዲዮን የተመለከቱ ሰዎች የተፈጠረባቸውን ድንጋጤ እና ቁጣ እየገለጹ ነው።
ይህ በሴቶች በተለይም በሕጻናት ላይ የሚፈጸመው የመድፈር ወንጀል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተደጋገመ መሆኑን ባለፉት ዓመታት የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
በዚህም ሳቢያ ወላጆች የልጆቻቸው ደኅንነት በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ነው።












