ህንዳውያኑ የጽዳት ሰራተኞች በጋራ በገዙት ሎተሪ 1.2 ሚሊዮን ዶላር አሸናፊ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Arun Chandrabose
በደቡባዊቷ ህንድ ኬራላ ግዛት 11 የጽዳት ሰራተኞች በጋራ የገዙት ሎተሪ የ100 ሚሊዮን ሩፒ (1.2 ሚሊዮን ዶላር) ዕጣ አሸናፊ አደረጋቸው።
ሰራተኞቹ ከወር በፊት ገንዘብ አሳባስበው በጋራ የገዙት ሎተሪ አሸናፊ እንዳደረጋቸው ያወቁት ባለፈው ሳምንት ነው።
የጽዳት ሰራተኞቹ በኬራላ ግዛት ማላፑራ አውራጃ የማይበሰብሱ ቆሻሻዎችን ከቤት ቤት በመሰብሰብ በሚያገኟት ገንዘብ ነው ኑሯቸውን የሚመሩት።
ቤቶች ከሚከፍሉት ወርሃዊ ክፍያ በቀን ወደ 250 ሩፒ (3 ዶላር) የሚያገኙ ሲሆን በተጨማሪም የሚሰብስቡት ቆሻሻን የሚሸጠው ድርጅት ከሚያገኘው ገንዘብ የተወሰነ ድርሻ ያገኛሉ።
ከዚህ የሚያገኙት ገንዘብ ኑሯቸውን ለመግፋት በቂ እንዳልሆነ የሚናገሩት ግለሰቦቹ አብዛኛዎቹም ለልጆቻቸው የትምህርት ክፍያ እና ለሌሎች ወጪዎች ብድር ወስደዋል።
ለዚያም ነው የሎተሪ ቲኬት በጋራ አሰባስበው የሚገዙት።
ሎተሪው በበርካታ የህንድ ግዛቶች ውስጥ ህገወጥ ቢሆንም የኬራላ አስተዳዳር በጣም ታዋቂ የሆነ የሎተሪ ዕጣ ፕሮግራም አለው። ግዛቲቷ የግል ሎተሪ ዕጣዎችን አግዳለች።
“በአንድ ወቅት የአንድ ሺህ ሩፒ ሽልማት አሸንፈን ተካፍለናል” በማለትም አብዛኛውን ጊዜ ለቡድኑ ቲኬቶችን የሚገዙት ኤምፒ ራድሃ ይናገራሉ።
ባለፈው ወር ቡድኑ በበዓላት ወይም በፌስቲቫሎች ወቅት ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኘውን ሎተሪ ለመግዛትም ቡድኑ 250 ሩፒ (3 ዶላር) ለማሰባሰብ ወሰነ።
የ72 ዓመቷ ኩቲማሉ እንደሚሉት ለሎተሪው የሚያዋጡት በቂ ገንዘብ ስላልነበራቸው አዝነው እንደነበር ተናግረዋል።
ከዚያም ሌላኛዋ የጽዳት ሰራተኛ ግማሹን ፣ 12.5 ሩፒ አበድረዋቸዋቸው ነው ለሎተሪው ያዋጡት። ሁለቱ የጽዳት ሰራተኞች እያንዳንዳቸው 12.5 ሲያዋጡ ሌሎቹ ዘጠኙ ደግሞ 25 ሩፒ አዋጥተዋል።
“ምንም ነገር ካሸነፍን እኩል እንደምንካፈል ተስማምተን ነበር። ነገር ግን ይህንን ያህል ትልቅ ገንዘብ እናሸንፋለን ብለን በጭራሽ አልጠበቅንም” ብለዋል ኩቲማሉ
የበዓላትን ዕጣ ሲገዙ አራተኛ ጊዜያቸው ሲሆን በአራተኛው ዕድለኛ በመሆናቸው ደስታቸው ከመጠን በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።












