የሕንድ የቀድሞ ፖለቲከኛ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ በጥይት ተመትተው ተገደሉ

ታትሟል

በአፈና ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው የነበሩት የቀድሞው የሕንድ ፖለቲከኛ በቀጥታ የቴሌቭዥን ቃለመጠይቅ እየሰጡ ሳለ ከወንድማቸው ጋር በጥይት ተመትተው ተገደሉ።

በፖሊስ ታጅበው የነበሩት አቲቅ አሕመድ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እየሰጡ ነበር ሽጉጥ ጭንቅላታቸው ላይ ተደግኖ ፕራያግራጅ ወይም አልላባድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገደሉት።

ከቅዳሜ ምሽቱ ግድያ በኋላ ጋዜጠኞች መስለው በስፍራው የተገኙ ሦስት ሰዎች በፍጥነት እጃቸውን ለፖሊስ ሰጥተዋል።

የአሕመድ ታዳጊ ልጅ ከቀናት በፊት በፖሊስ ተገድሎ ነበር።

አቲቅ አህመድ ባለፉት ሃያ አመታት ውስጥ አፈና፣ ግድያ እና ዝርፊያን ጨምሮ ከበርካታ ጉዳዮች ጋር ስማቸው ይነሳል። የአካባቢው ፍርድ ቤት በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በእርሳቸው እና በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ ከአፈና ጋር በተያያዘ በተመሠረተባቸው ክስ የዕድሜ ልክ እስራት አስተላልፎባቸዋል።

አህመድ ቀደም ሲል በፖሊስ ለገደል እችላለሁ በማለት ለሕይወታቸው እንደሚሰጉ ተናግረው ነበር።

እጃቸው በካቴና የታሰረው አሕመድ እና ወንድማቸው አሽራፍ ለህክምና ክትትል ወደ ሆስፒታል ሲያቀኑ ነበር ከጋዜጠኞች የቀረቡላቸው ጥያቄዎች እየመለሱ የነበረው።

በማህበራዊ ሚዲያ እና በቴሌቭዥን ጣቢያዎች በሰፊው በተሰራጨው ቃለ መጠይቅ አሕመድ በተገደለው ልጃቸው የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው እንደሆነ ተጠይቀዋል።

ከግድያው በፊት ለጋዜጠኞች የተናገሩት የመጨረሻ ቃልም "እነሱ ስላልወሰዱን አልሄድንም" የሚል ነበር።

ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በሞተር ሳይክሎች በቦታው መድረሳቸውን ፖሊስ ተናግሯል። በጥቃቱ ስፍራ አንድ ፖሊስ እና አንድ ጋዜጠኛም ቆስለዋል።

የቅዳሜ ምሽቱን ግድያ ተከትሎ ዋና ሚኒስተር ዮጊ አድቲያናት በግድያው ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ከመስጠት ባለፈ ሠላምን ለማረጋገጥ በኡታር ፕራዴሽ ግዛት ውስጥ ትላልቅ ስብሰባዎችን አግደዋል።

በመገናኛ ብዙሃን እና በፖሊስ ፊት አንድ ሰው እንዴት ሊገደል ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች ጥያቄዎችን አንስተዋል። የቢቢሲ ሂንዲ ዘጋቢ አናንት ዛናን በከተማዋ ያለው ሁኔታ የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለ እንደሚመስል ዘግቧል።

አቲቅ አሕመድ ማን ነበሩ?

በፖለቲካም ሆነ ከወንጀል ደርጊት ጋር በተያያዘ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ጉዞ አላቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ በግድያ የተጠረጠሩት እአአ በ1979 ነበር። ቀጥሎ ባሉት 10 ዓመታት በአላሃባድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን በቁ።

የመጀመርያ ምርጫውን የግል እጩ ሆነው በመወዳደር በ1989 አሸንፈው የክልል ህግ አውጪ ሆኑ። ለሁለት ተከታታይ ጊዜያትም ወንበሩን አሸነፉ። አራተኛው ድል ሳማጃዋዲ ፓርቲን (ኤስፒ) በመወከል አሳኩ።

አሕመድ እአአ በ 2019 የሕንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጉጃራት ግዛት ውስጥ ወደሚገኝ እስር ቤት እንዲዛወሩ ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ያስተላለፈው በሌላ ጉዳይ ላይ ፍርድ በመጠባበቅ ላይ ከነበሩበት ከኡታር ፕራዴሽ እስር ቤት በአንድ ነጋዴ ላይ ጥቃት ለማድረስ ማቀዳቸው ከታወቀ በኋላ ነው።

ፖሊስ ለሕይወቴ ያሰጋኛል ሲሉ አሕመድ ባለፈው ወር ለሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት አላገኘም።

ኡታር ፕራዴሽ ግዛት የሚተዳደረው በሂንዱ-ብሔርተኛው ቢጄፒ ፓርቲ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግድያውን የጸጥታ ጉድለት ሲሉ ተችተዋል።

የተቃዋሚው ሳማጃዋዲ ፓርቲ ኃላፊ አኪሌሽ ያዳቭ በትዊተር ገፃቸው “በኡታር ፓዴሽ ውስጥ ወንጀል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። የወንጀለኞች ሞራልም ከፍ ያለ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

በዚህ ግዛት ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች የተጠረጠሩ ከ180 በላይ ሰዎች በፖሊስ ተገድለዋል።

የመብት ተሟጋቾች ፖሊስ ከፍርድ ቤት ውጭ ግድያ ፈጽሟል ሲሉ ቢከሱም የግዛቲቱ አስተዳዳሪዎች ውድቅ ያደርጉታል።