ጭልፊት እጃቸው ላይ እባብ የጣለባቸው የቴክሳሷ ነዋሪ ጉዳት ደረሰባቸው

ታትሟል

በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ነዋሪ የሆኑት የ64 ዓመት አዛውንት በማይጠበቅ አጋጣሚ ጭልፊት እጃቸው ላይ እባብ ከጣለ በኋላ በተሳቢው እንስሳ እና በጭልፊቱ ጥቃት ደረሰባቸው።

ፔጊ ጆንስ የግቢያቸውን ሳር እያጨዱ ሳለ ነበር እባብ ይዞ ከላይ እየበረረ የነበረ ጭልፊት የያዘው ተሳቢ እንስሳን ድንገት እጃቸው ላይ የጣለው።

የፔጊ እጅ ላይ የወደቀው እባብ ግራ እጃቸው ላይ በፍጥንት ተጠምጥሞ እጃቸውን እና ፊታቸውን እያጠቃ ባለበት ተመሳሳይ ሰዓት ለምግብነት የያዘው እባብ የተነጠቀው ጭልፊት ደግሞ የ64 ዓመቷን አዛውንት ከለይ ታች ያጣድፋቸው ያዘ።

ፔጊ አጋጣሚውን ሲገልጹ እጃቸው ላይ ድንገት የወደቀውን እባብ ከማንሳታቸው በፊት ጭልፊቱ ያጠቃቸው እንደጀመረ ይናገራሉ።

ይህ ያልተጠበቀው አጋጣሚ ግራ እጃቸው ላይ መቆራረጥ፣ መላላጥ እና ትልቅ ብልዝ የፈጠረ ሲሆን ፊታቸው ላይ ጉዳት እንዲፈጠር አድርጓል።

አጋጣማዊው የተከሰተው ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በቴክሳስ ግዛት ሲልስቢ ተብላ በምትጠራ ከተማ ሲሆን፤ “እባቡን ከእጄ ላይ ላራግፈው ስጥር እጄ ላይ ተጠመጠመ። እባቡ ፊቴን እየነደፈኝ ነበር . . . ከአንዴም ሁለት ግዜ መነጽሬን ነክሶታል። ደግሜ ደጋግሜ ከእጄ ላይ ልወረውረው ብሞክርም ከላዬ ላላቅቀው አልቻልኩም” በማለት የነበረውን ሁኔታ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

ፔጊ ዛፍ ስር አለመቆማቸውን በማሰብ እባቡ ምናልባት ከወፍ እጅ የወደቀ መሆኑን እያሰቡ ትግል ላይ ሳሉ ጥርጣሬያቸው ትክክል ሆኖ ድንገት ጭልፊት ግብግቡ ውስጥ ከባ።

“ጭልፊቱ እጄ ላይ የተጠመጠመውን እባብ ቆንጥጦ ይዞ መጎተት ጀምረ። እባቡን ሲጎትት እጄን አብሮ ወደላይ መጎተት ጀመረ” ይላሉ ፔጊ።

ምግቡን በፔጊ ጆንስ የተነጠቀ የመሰለው ጭልፊት በጥፍሮቹ በተደጋጋሚ ግራ እጃቸው ላይ ጉዳት አድርሷል።

ፔጊ እጅ እና ፊታቸው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማረ መነጽራቸው መሰበሩን ገልጸው የደረሰባቸው ጥቃት ትልቅ ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው ጨምረው ተናግረዋል።

በመጨረሻም ጭልፊቱ እባበቱን ከአዛውንቷ እጅ ነጥቆ በሮ ሄዷል።

ጉዳት የደረሰባቸው አዛውንትም ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።