ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ሸሹ
ሩሲያ በሰሜን ምሥራቅ ዩክሬን ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መሸሻቸው ተገለጸ።
ካሪኪቭ ከተባለው አካባቢ ወደ 1,800 ነዋሪዎች መውጣታቸውን የአካባቢው አስተዳደር አስታውቋል።
ያሳለፍነው አርብ ሩሲያ ድንገት ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ ድንበር አካባቢ ውጊያ ተካሂዷል።
ከሰሞኑ ከሩሲያ ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል ዩክሬን እየጠበቀች ነበር። ካሪኪቭ ከተማን ለመቆጣጠር ሩሲያ እንደምትሞክርም ተገምቶ ነበር።
ከተማዋ የዩክሬን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ናት። የሩሲያን ጥቃት ወታደሮቿ እንደመከቱት ዩክሬን ገልጻለች።
ሩሲያ በበኩሏ አምስት መንደሮች እንደተቆጣጠረች አስታውቃለች።
ቢቢሲ ይሄንን በገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ሩሲያ ምን ያህል ገፍታ እንደምትሄድ አልታወቀም። ይሄ ጥቃት የአንድ ጊዜ ይሁን ወይም ቀጣይነት ያለው መሆኑም ግልጽ አይደለም።
ዩክሬን የአፀፋ ምላሽ እየሰጠች ነው። 1,775 ነዋሪዎች እንዲወጡ ተደርጓል።
የከተማው አስተዳዳሪ ኦሌህ ሲዬህቦቭ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ከተማዋ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሼሪ የተባለ የከተማው ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ በሩሲያ ቦምብ ቤቱና መኪናው ወድሟል።
ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ባለቤቱን ወደ ሆስፒታል መወሰዷን ገልጿል።
አራቱ ፍየሎቻቸው ላይ ምን እንደሚደርስባቸው ስላላወቀ ጥሎ ለመውጣት እንደተቸገረ ተናግሯል።
የሩሲያ ኃይል እያደረሰ ያለው ጥቃት ከፍተኛ ሲሆን እስካሁን ከዩክሬን በኩል ምላሽ አልተሰጠም።
የዩክሬን ባለሥልጣኖች እንዳሉት ሩሲያ ውጊያውን በድንበር አካባቢ ለማስፋፋት ልትሞክር ትችላለች።
ሩሲያ የዩክሬንን ድንበር በመጣስ የምታደርገው ጥቃት ዓላማው ቤልጎርድ ለተባለው ግዛቷ ወደ 10 ኪሎሜትር ነጻ ቀጠና መፍጠር እንደሆነ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ፣ በሰባት የድንበር መንደሮች ውጊያ መቀጠሉን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
“የመከላከል ኦፕሬሽናችን በካሪኪቭ ቀጥሏል” ብለዋል።
አሜሪካ አዲስ የ400 ሚሊዮን ዶላር የመሣሪያ ድጋፍ ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
ለዩክሬን የመሣሪያ ድጋፍ የመስጠት ጉዳይ ባስነሳው ፖለቲካዊ ውዝግብ ምክንያት ለወራት ድጋፍ ሳይሰጥ ቢቆይም አሁን ሦስተኛ ዙር ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እንዳሉት፣ በአስቸኳይ የሚያስፈልገው ድጋፍ የአየር መከላከያ፣ የታንክ መቃወሚያ፣ የጦር ተሽከርካሪና ሌሎችም መሣሪያዎችን የያዘ ነው።
የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፣ ሩሲያ “በቀጣይ ሳምንታት ወደ ዩክሬን ግዛት በመግባት ነጻ ቀጠና ለመፍጠር ትሞክራለች” ብለዋል።
የአሜሪካ የመሣሪያ ድጋፍ መዘግየቱን ሩሲያ ልትጠቀምበት ትፈልጋለች። በዚህ ወቅት ወደ ዶንቴስክ ግዛት የመግባትም ዕቅድ እንዳላት መረዳት ይቻላል።