የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ በሙስና የተጠረጠሩ አባላቱን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባላት ላይ ከቀረበው የሙስና ክስ ጋር የሁለት የምክር ቤት አባላቱን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት አስፈላጊውን ሂደት ሊያካሂድ እንደሆነ አሳወቀ።
የፓርላማው ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜሶላ እንደተናገሩት የኅብረቱ ምክር ቤት ይህንን እርምጃ የሚወስደው ከቤልጂየም ፖሊስ የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ ነው።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቷ ይህ ያለመከሰስ መብት መነሳት የሚመለከታቸው የምክር ቤቱ አባላትን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ይህ ቅሌት ይፋ የሆነው ባለፈው ወር አራት የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባላት በሙስና እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ በማድረግ ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ነው።
ባለሥልጣናት ከምክር ቤት አባላቱ የወንጀል ድርጊት ጋር የተያያዘው የትኛው አገር እንደሆነ ያልጠቀሱ ቢሆንም፣ በርካታ ምንጮች ግን ጉቦ ከመስጠት ድርጊት ጋር በተያያዘ ኳታርን እያነሱ ይገኛሉ።
የባሕረ ሰላጤዋ ሀብታም አገር ኳታር ግን ከሙስና ድርጊቱ ጋር ስሟ መነሳቱ “በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት አስተባብላለች።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሜሶላ፣ በኅብረቱ ውስጥ የተከሰተው ቅሌት “ለነጻ፣ ግልጽ እና ዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰቦች በጥቃት ውስጥ” መሆናቸውን የሚያሳይ ነው በማለት፣ በፖሊስ ጥያቄ መሠረት የአባላቱን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት “አስቸኳይ ሂደት” እንደሚጀመር ገልጸዋል።
በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፖሊስ ለምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ጥያቄ ያቀረበው ባለፈው አርብ ነው።
ጥያቄው ከሁለት ሳምንት በኋላ በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ከታየ በኋላ ለምክር ቤቱ የሕግ ጉዳዮች ኮሚቴ ይቀርባል። ከዚያ በኋላም ዝርዝር ሪፖርት ለምክር ቤቱ ቀርቦ የአባላቱ ያለመከሰስ መብት ላይ ድምጽ የሚሰጥ ይሆናል።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት እንዳሉት ይህ ሂደት በአንድ ወር ውስጥ እንዲጠናቀቅ ይፈልጋሉ።
የአውሮፓ ኅበረት ፓርላማ አባላት ሥራቸውን ካለምንም ስጋት እና ተጽዕኖ እንዲያከናውኑ ከእስር እና ከፖለቲካዊ መሳደድ ለመጠበቅ የሚያስችል የተወሰነ ደረጃ ያለው ያለመከሰስ መብት አላቸው።
ነገር ግን በወንጀል የተጠረጠሩ የምክር ቤቱ አባላት ማስረጃዎችን በማቅረብ እራሳቸውን ለመከላከል በሚችሉበት ሁኔታ በምክር ቤቱ በሚካሄድ ምሥጢራዊ ሂደት ያለመከሰስ መብታቸው ሊነሳ ይችላል።
ከዚህ የሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ ባለፈው ወር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከኅብረቱ ምክር ቤት አባላት መካከል ግሪካዊቷ የምክር ቤት አባል ኤቫ ካይሊ አንዷ ናቸው።
የ44 ዓመቷ የምክር ቤት አባል ምንም ጥፋት አለመፈጸማቸውን ቢገልጹም፣ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል። ግለሰቧ በትልቅ ሻንጣ የታጨቀ ገንዘብ እንደተያዘባቸው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ሪፖርት ተደርጓል።
በቤታቸው ውስጥ 150,000 ዩሮ ከተገኘ በኋላ ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው ሪፖርቶች የወጡ ቢሆንም ጠበቃቸው ግን ይህንን አስተባብሏል።
ምንጮች እንዳሉት በሌሎች ተጠርጣሪዎች ቤት እና የሆቴል ክፍል ውስጥ 600,000 እና 750,000 ዩሮ በቦርሳ ውስጥ ታጭቆ ተገኝቷል።
የቤልጂየም መንግሥት የደኅንነት አገልግሎት እንዳሳወቀው ከአውሮፓ አገራት ጋር በመተባበር በኅብረቱ ምክር ቤት አባላት ላይ ለቀረበለት የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ምርመራ ሲያካሂድ ነበር።












