ሚስቱን ዋስትና በከለከሉበት ፖሊስ ችሎት ላይ በጥይት የተመቱት ዳኛ ሕይወት አለፈ

ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ከቀናት በፊት ችሎት ላይ ሳሉ በአንድ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን ተተኩሶባቸው ቆስለው የነበሩት ኬንያዊት ዳኛ ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አስታወቁ።

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ የሆኑት ማርታ ኩሜ በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚገኘው የማካዳራ ዋና ችሎት ዳኛ የነበሩት ሞኒካ ኪቩቲ “ከደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ለማገገም አልቻሉም” ብለዋል።

ዳኛዋ ችሎት ላይ በአንድ የፖሊስ መኮንን በጥይት የተመቱት ባለፈው ሐሙስ፣ የፖሊሱ ሚስት ችሎት ለመቅረብ ፈቃደኛ ስላልነበረች ያቀረበችው የዋስትና ጥያቄን ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ዳኛዋ ላይ ችሎት ውስጥ ተኩስ የከፈተው የፖሊስ መኮንን ሳምሶን ኪፕቺርቺር ኪፕሩቶ የተባለ ሲሆን፣ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ በስፍራው በነበሩ ፖሊሶች ተተኩሶበት ተገድሏል።

በተኩስ ልውውጡ ወቅት ተጨማሪ ሦስት የፖሊስ መኮንኖች የቆሰሉ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ሁሉም በደህና ሁኔታ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

“ክብርት ዳኛ ሞኒካ ኪቩቲ ፍርድ ቤት ውስጥ ከተፈጸመባቸው ከባድ ጥቃት ሊያገግሙ እንዳለቻሉ ለኬንያ ሕዝብ ስገልጽ በከባድ ሐዘን ውስጥ ሆኜ ነው” ብለዋል የአገሩቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ ዛሬ ቅዳሜ ባወጡት መግለጫ።

“የአገሪቱ ሁሉም የሕግ ተርጓሚ አካል አባላት በዚህ አሳዛዥ ጊዜ በመተዛዘን በጋራ እንቁም” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ስታር የተሰኘው ጋዜጣ የሆስፒታል ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በጥይት ደረታቸውን እና እግራቸውን ተመትተው ናይሮቢ ሆስፒታል ገብተው የነበሩት ዳኛ ሕይወታቸው ያለፈው ከጥቃቱ አንድ ቀን በኋላ አርብ ዕለት ነው።

በዳኛዋ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛዋ ድርጊቱ የተፈጸመበት ችሎት አስከ መጪው ሰኞ ድረስ ዝግ እንዲሆን አዘዋል።

የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ጥቃቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ዳኛዋ ላይ የተኮሰው የፖሊስ መኮንን በምዕራብ ኬንያ ውስጥ የሚገኝ ሎንዲያኒ የተባለ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ የነበረ ሲሆን፣ የሚስቱ ጉዳይ በሚታይበት ችሎት ላይ እንዴት ሊገኝ እንደቻለ የታወቀ ነገር የለም ብሏል።

ተከሳ የዋስትና መብት የተከለከለችው የፖሊስ መኮንኑ ሚስት “በሐሰተኛ መንገድ” ገንዘብ በመቀበል ተከሳ ነበር ችሎት የቀረበችው።

ለዳኛዋ እና ለሦስት ፖሊሶች መቁሰል ምክንያት የሆነውን ጥቃት ለማጣራት ምርመራው እንደቀጠለ መሆኑም ተጠቅሷል።

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ኩሜ ግን የፖሊስ መኮንኑ ዳኛዋን ለመግደል ዕቅድ እንደነበረው ግልጽ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ በፍርድ ቤት ውስጥ በዳኛ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ኬንያውያን አስደንግጧል።

የአገሪቱ ፖሊስ ያለፍርድ ግድያዎችን በመፈጸም በተደጋጋሚ ቢከሰስም፣ በፍርድ ቤት ውስጥ እንደዚህ ያለ ክስተት ግን አጋጥሞ አያውቅም ተብሏል።

የአገሪቱ የፍትህ ቢሮ የደኅንነት አጠባበቁን እንደሚያጠናክር ገልጾ፣ የፍትህ ሠራተኞች እና ሌሎች የፍርድ ቤት ተገልጋዮች ደኅንነት እንደሚጠበቅም አረጋግጧል።

የኬንያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ባወጣው መግለጫ ይህ ሁኔታ “አንድ ነጠላ ክስተት አይደለም፣ ነገር ግን በዳኞች እና በጠበቆች ላይ አሳሳቢ የሆነው የመጣው ስጋት እና ጥቃት አንድ አካል ነው” በማለት ድርጊቱ አዲስ አይደለም ብሏል።