በዜግነቷ ምክንያት መነጋገሪያ ሆና የቆየችው ሴት ከደቡብ አፍሪካው የቁንጅና ውድድር ራሷን አገለለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዜግነቷ ምክንያት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆና የቆየችው ደቡብ አፍሪካዊት ከሀገሪቱ የቁንጅና ውድድር ራሷን ማግለሏን አስታውቀች።

ተወዳዳሪዋ ይህን ውሳኔ የወሰነችው ለራሷ እና ለቤተሰቦቿ ደኅንነት ስትል መሆኑን ገልጣለች።

ቺዲማ አዴትሺና በኢንስታግራም ገጿ ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን ከማሳወቋ ከአንድ ቀን በፊት የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር በከፈተው ምርምራ እናቷ የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ለማግኘት “የማንነት ማጭበርበር” ሳትፈፅም አትቀርም ብሏል።

የሕግ ተማሪ የሆነችው የ23 ዓመቷ አዴትሺና ከጆሀንስበርግ ወጣ ብላ በምትገኘው ሶዌቶ እንደተወለደች የምትናገር ሲሆን ያደገችው ደግሞ በኬፕ ታውን ከተማ ነው።

ከዚህ ቀደም በሰጠቻቸው ቃለ-ምልልሶች አባቷ ናይጄሪያዊ እንደሆነ እናቷ ደግሞ የሞዛምቢክ ደም ያለባት ደቡብ አፍሪካዊት እንደሆነች ተናግራለች።

ላለፉት ሳምንታት የተወዳዳሪዋ ማንነት በተለይ በማኅበራዊ ሚድያዎች የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ የቆየ ሲሆን አንዳንድ ደቡብ አፍሪካዊያን አዴትሺና ደቡብ አፍሪካዊ አይደለችም የሚል ሐሳብ ሲያሰሙ ነበር።

ሁኔታዎች እየተካረሩ ሲመጡ ነው የሚስ ደቡብ አፍሪካ አዘጋጅ ኮሚቴ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ምርመራ እንዲያደርግ የጠየቀው።

የሚስ ደቡብ አፍሪካ የቁንጅና ውድድር ቅዳሜ ይካሄዳል።

ሚኒስቴሩ ረቡዕ ዕለት በለቀቀው መግለጫ እስካሁን ባደረገው ምርመራ የአንዲት “ምስኪን” ደቡብ አፍሪካዊት ማንነት በኤትሺና እናት “ሳይሰረቅ አይቀርም” ብሏል።

መግለጫው አክሎ “ነገር ግን ቺዲማ በዚህ ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት ላይ ልትሳተፍ አትችልም፤ ምክንያቱም በወቅቱ እሷ ገና ጨቅላ ነበረች” ብሏል።

ሚኒስቴሩ ተጨማሪ ምርመራ ካደረገ በኋላ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን አጣቅሶ ክስ ሊመሠርት እንደሚችል አስታውቋል።

እናቷ በተጠረጠረችበት ድርጊት ዙሪያ “የአዴትሺና ዜግነት ላይ ምን ዓይነት አንድምታ ይኖረዋል?” የሚለውን ሕግ አጣቅሶ እንዲመረምርም ገልጧል።

አዴትሺና በኢንስታግራም ገጿ ባስተላለፈችው መልዕክት ስለእናቷ ጉዳይ ምንም አላለችም። ነገር ግን ከውድድሩ ራሷን ለማግለል መወሰኗ “እጅግ ከባድ” እንደሆነ አስታውቃለች።

ከወዳጅ ዘመዶቿ ለደረሳት “ፍቅርና ድጋፍ” ምስጋና የለገሰችው ኤደትሺና ለተቀሩት የቁንጅና ተወዳዳሪዎች መልካም ዕድል ተመኝታለች።

“ዙፋኑን የምታነሳው ሴት ሁላችንንም የምትወክለን ትሆናለች” ብላለች።