ባለፉት ሁለት ሳምንታት ሰፊ ቦታ ከሩሲያ አስለቅቀናል -ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ

ታትሟል

የዩክሬን ጦር የመልሶ ማጥቃት ዘመቻውን በመቀጠል ከሩሲያ ተጨማሪ መሬቶችን መያዙን የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

ቮሎዲሚር ዜለንስኪ እንዳሉት ወታደሮቻቸው ባለፉት ሁለት ሳምንታት በምስራቅ እና በደቡብ የሃገሪቱ ክፍሎች በሩሲያ ቁጥጥር ስር ከነበሩ ቦታዎች ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን የመሬት ይዞታ በድጋሚ መቆጣጠር  ችለዋል።

ቢቢሲ ፕሬዚዳንቱ በቁጥጥራችን ስር ናቸው ያሏቸውን የመሬት ይዞታ አሃዝ ማረጋገጥ አልቻለም።

ሩሲያ በሰሜናዊ ምስራቅ ካርኪቭ ክልል ቁልፍ ከተሞችን ማጣቷን አምናለች። በአንዳንድ ወታደራዊ ባለሙያዎች ይህ የጦርነቱ ትልቅ ስኬት ተብሎ ተወስዷል።

ሞስኮ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ወታደሮቿን ከአካባቢው በማስወጣት በዩክሬን ምስራቃዊ ክፍል በሉሃንስክ እና ዶኔትስክ ክልሎች ላይ ለማተኮር “እንደገና የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነች” መሆኗን ገልጻለች።

ይህንን ገለጻ በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጭምር ተሳልቀውበታል። ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች “አሳፋሪ” ሲሉ ገልጸውታል።

ሰኞ አመሻሽ ላይ ከቢቢሲ ቆይታ ያደረጉት የኢንስቲቲዩት ፎር ዘ ስተዲ ኦፍ ዋር ባልደረባ የሆኑት ሜሰን ክላርክ በርካታ መሳሪያዎቻቸውን ትተው ለመውጣት መገደዳቸው ለሩሲያ ወታደሮች  “ሙሉ ጥፋት” ነው ብለዋል።

በመጋቢት መጨረሻ በዋና ከተማዋ ኪዬቭ አቅራቢያ የተተካሄደው ዘመቻ ከከሸፈ በኋላ ይህ በጣም ትልቁ የሩሲያ ወታደራዊ ማፈግፈግ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር የዩክሬን ኃይሎች በመልሶ ማጥቃት “ትልቅ ዕድገት” ማስመዝገባቸውን ገልጸው ውጤቱን ለመተንበይ ግን ገና ነው ብለዋል።

"ሩሲያውያን በዩክሬን ውስጥ በጣም ትልቅ ኃይል እና የጦር መሳሪያዎችን ይዟል። እንዳየነውም ይህንንም በዩክሬን ታጣቂ ኃይሎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሲቪሎች እና በሲቪል መሠረተ ልማት ላይ መጠቀሙን ቀጥለዋል" ብለዋል ብሊንከን።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአውሮፓውያኑ የካቲት 24 ዩክሬንን ጦራቸው ሙሉ በሙሉ እንዲወሩ አዘዙ።

ሩሲያ አሁንም ከሃገሪቱ አንድ አምስተኛውን በቁጥጥሯ ስር አድርጋለች። ሰኞ ምሽት ባደረጉት የቪዲዮ ንግግር ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ “ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተዋጊዎቻችን በምስራቅ እና በደቡብ ከሚገኙ የዩክሬን ግዛቶች ከ 6,000 ካሬ ኪሎ ሜትር (600 ሺህ ሄክታር) በላይ የሚሆነውን ነፃ አውጥተዋል” ብለዋል።

"የወታደሮቻችን እንቅስቃሴ ቀጥሏል" ሲሉ አክለዋል።

መልሶ ማጥቃቱ ፈጣን የሆነ ይመስላል። ባለፈው ሐሙስ ፕሬዝደንት ዜለንስኪ የዩክሬን ጦር 1,000 ካሬ ኪሎ ሜትር መልሶ መያዙን ገልፀው ነበር። በእሑድ ዕለት ይህ ቁጥር በሦስት እጥፍ ወደ 3,000 ካሬ ኪ.ሜ አድጓል።

ዜለንስኪ በመልሶ ማጥቃት የተሳተፉትን የዩክሬን ብርጌዶችን አመስግነዋል። ተዋጊዎቻቸውንም “እውነተኛ ጀግኖች” በማለት አሞግሰዋል።

የትኞቹ የዩክሬን ከተሞች እና መንደሮች ነፃ እንደወጡ ግን አልገለጹም።

የራሺያ ጦር ወታደሮቿ በካርኪቭ ክልል ከሚገኙትና ቁልፍ ከሆኑት ባላክሊያ፣ ኢዚዩም እና ኩፒያንስክ መውጣታቸውን ቀደም ብሎ አምኗል። በምስራቅ አቅጣጫ ሩሲያ አሁን የምትቆጣጠረው ትንሽ ቦታ ብቻ ነው።

ዘገምተኛ ቢሆንም የዩክሬን ወታደሮች ከክሬሚያ ጋር በሚያዋስነው የደቡብ ኬርሰን ክልል ወደ ፊት መጓዙን ቀጥሏል። 

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ባለስልጣናት የዩክሬን ጦር በቅርብ ጊዜ ያስመዘገባቸው ስኬቶች ለሩሲያ አጠቃላይ ዕቅድ ትልቅ ትርጉም ይኖራቸዋል ብለዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በዩክሬን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች "መጀመሪያ ላይ የተቀመጡት ሁሉም ተግባራት እስኪፈጸሙ ድረስ" እንደሚቀጥሉ አጥብቀው ተናግረዋል።

ሩሲያ ከቅርብ ቀናት በፊት በዩክሬን ተመልሶ በተወሰዱ አካባቢዎች ሠራዊቷ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ገልጻለች።

የኢዚዩም ከንቲባ ቫለሪይ ማርቼንኮ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የዩክሬን ጦር በከተማው ውስጥ እንዳለ እና የሃገሪቱ ባንዲራ መሰቀሉን አሳውቀዋል።

ሰራዊቱ በጦርነት የተመሰቃቀለችውን ከተማ በማጽዳት ላይ ሲሆኑ በሰዎች ቤት ውስጥ ሊደበቁ የሚችሉ የሩሲያ ወታደሮችንም በማፈላለግ ላይ ይገኛሉ።

ማርቼንኮ ከ"10 ቀናት ገደማ" በኋላ ከተማዋን ለቀው ለመውጣት የተገደዱ ነዋሪዎች መመለስ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

ሩሲያ በጦር ሜዳው ላይ የተፈጠረው ሽንፈት ለመበቀል የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ አድርጋለች በሚል ትከሰሳለች።

እሑድ ዕለት የተካሄዱ የሚሳኤል ጥቃቶች በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ከፍተኛ የሃይል መቆራረጥ ተከስቷል።

 በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መብራት እና ውሃ ለበርካታ ሰዓታት አጥተው ቆይተዋል።