ግሌዘሮች ለክለቡ 'ደንታ የላቸውም’፤ ኔቪል እና ሩኒ ጓደኞቼ አይደሉም- ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የማንቸስተር ዩናይትዱ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የክለቡ ባለቤቶች የሆኑት የግሌዘር ቤተሰቦች ከስፖርት አኳያ ከታየ “ስለክለቡ ምንም ደንታ የላቸውም” ሲል ገለጸ።
ሮናልዶ ክለቤ “ከዳኝ” ብሎ ለቶክ ቲቪ የሰጠው ቃለ መጠይቅ መነጋገሪያ ሆኗል። የቃለ ምልልሱ ሌላኛው ክፍል ሰኞ ምሽት ተለቋል።
"ማንችስተር ንግድ ክለብ ነው፤ ከገበያ ገንዘብ ያገኛሉ" ሲል ተናግሯል።
"በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ማንቸስተር ሜዳ ላይ የበላይ ለመሆን ከባድ ይሆንበታል" ብሏል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የ37 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ የፊት መስመር ተጫዋች "የክለቡ ባለቤቶች የሆኑት ግሌዘሮች ስለ ክለቡ ደንታ የላቸውም" ብሏል።
ሮናልዶ አክሎም በ2005 ክለቡን ከተረከቡት የግሌዘር ቤተሰብ አባለት ጋር ተገናኝቶ እንደማያውቅም ተናግሯል።
ዩናይትድ ለሮናልዶ ቃለ መጠይቅ ሰኞ ዕለት ምላሽ ሰጧል። ክለቡ "ማንቸስተር ዩናይትድ የክርስቲያኖ ሮናልዶን ቃለ መጠይቅ አስመልክቶ የሚዲያ ዘገባዎችን ተከታትሏል። ክለቡ ሙሉ መረጃዎች ከወጡ በኋላ የሚሰጠውን ምላሽ ግምት ውስጥ ያስገባል” ብሏል።
"ትኩረታችን ለሁለተኛው የውድድር አጋማሽ መዘጋጀት እና በተጫዋቾች፣ በአሰልጣኞች፣ በሠራተኞች እና በደጋፊዎች መካከል እየተገነባ ያለውን መነሳሳት፣ እምነት እና አንድነት ማስቀጠል ላይ ነው" ሲልም ክለቡ አክሏል።
እአአ በ2017 ለመጨረሻ ጊዜ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ያነሳውን ክለብ ባለቤቶች በመቃወም ደጋፊዎች በርካታ ተቃውሞዎችን አካሂደዋል።
የፖርቹጋሉ አምበል ሮናልዶ አክሎም "ደጋፊዎቹ ሁሌም ትክክል ናቸው። እውነታውን ማወቅ አለባቸው። ተጫዋቾቹ ለክለቡ ጥሩ ነገር ይፈልጋሉ። እኔም ለክለቡ ጥሩ ነገር እመኛለሁ። ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የመጣሁትም ለዚህ ነው። ለዚህም ነው ይህንን ክለብ የምወደው” ብሏል።
“ማንቸስተር እንደ ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና አሁን ደግሞ እንደ አርሴናል ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዳይደርስ የሚያደርጉ አንዳንድ ነገሮች በክለቡ ውስጥ አሉ።“
"ውስብስብ ነው። ከባድ ነው። በጣም ከባድ ነው።"
"ኔቪልና ሩኒ ጓደኞቼ አይደሉም"
በእሑዱ ቃለ ምልልስ ወቅት ሮናልዶ የቀድሞው የዩናይትድ የቡድን አጋሩ ዋይኒ ሩኒ ስለተቸው ተበሳጭቶ እንደሆን ተጠይቆ ነበር።
ሮናልዶ "ምናልባት በሠላሳዎቹ ዕድሜው ጫማውን ስለሰቀለ ይሆናል። እኔ አሁንም በትልቅ ደረጃ እየተጫወትኩ ነው። ከሱ የተሻልኩ ነኝ አልልም። ምክንያቱም እውነት ነው. . .።"
አሁን ደግሞ ትኩረቱን ወደ ሌላ የቀድሞ የዩናይትድ አጋሩ ጋሪ ኔቪል አዙሯል።
የቀድሞ የእንግሊዝ የቀኝ መስመር ተከላካይ በቅርቡ ለስካይ ስፖርት ተንታኝ ሆኖ ሲሠራ ሮናልዶ ሠላም ሳይለው ቀርቷል።
"ከአንተ ጋር ከተጫወቱ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ትችት እና አሉታዊነት ማዳመጥ በጣም ከባድ ነው። ለምሳሌ ጋሪ ኔቪል። ሁለቱም ጓደኞቼ አይደሉም" ሲል ሮናልዶ ተናግሯል።
"መተቸት ቀላል ነው። በቴሌቪዥን ሠርቶ የበለጠ ታዋቂ ለመሆን መተቸት ግዴታ ይሁንባቸው አላውቅም። በእርግጥም አልገባኝም።“
"ሞኞች ስላልሆኑ (የእኔን ስም) የሚያነሱት ሊጠቀሙበት ይመስለኛል። ከአንተ ጋር በአንድ መልበሻ ክፍል የነበሩ ሰዎች በዚያ መንገድ ሲተቹ ማየት በጣም ከባድ ነው" ብሏል።
ከዚህ በፊት ምን ተፈጠረ?
ቀደም ሲል በተለቀቀው የቃለ ምልልሱ ክፍል በሳምንት 500 ሺህ ፓውንድ የሚከፈለው ሮናልዶ ክለቡ አስገድዶ ሊያስወጣው እየሞከረ መሆኑን እና አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግን እንደማያከብር ተናግሯል።
ሮናልዶ ከአውሮፓውያኑ 2003 እና 2009 ለዩናይትድ 118 ጎሎችን አስቆጥሯል። በ2021 ክረምት ወደ ክለቡ በድጋሚ የተመለሰው በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ በአክብሮት ነበር። በዚህ ሳምንት የሚተላለፈው ሙሉው ቃለ መጠይቅ ብዙ ደጋፊዎችን ከእሱ እንደሚያርቅ ይጠበቃል።
ሮናልዶ አሁን በኳታር ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።












