ቻይና አሳሳቢ የነበረውን የታዳጊዎች የቪዲዮ ጌም ሱሰኝነት ለመግታት ችያለሁ አለች

ታትሟል

በበርካታ ቻይናውያን ታዳጊዎች ዘንድ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ የነበረው የቪዲዮ ጌም ሱሰኝነት መገታቱን አንድ ጥናት አመለከተ።

ይህ ሪፖርት የወጣው ከጌም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከሚቆጣጠረው አካል ጋር ግንኙነት ያለው የቻይና የቪዲዮ ጌሞች አምራ ቡድን ነው።

ይህም በአንድ ወቅት ለታዳጊዎች “መንፈሳዊ ዕጽ ነው” በሚል ከፍተኛ ቁጥጥር ሲደረግበት የነበረውን የቪዲዮ ጌም ዘርፍ ላይ የመንግሥት ኃላፊዎች የጣሉትን ጥእብቅ ቁጥጥርን ያላላሉ የሚል ተስፋን ጭሯል።

ካለፈው የፈረንጆች ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ ህጻናት በሳምንት ከሦስት ሰዓታት በላይ ጌም ላይ እንዳያሳልፉ ታግደዋል።

የቻይና ባለሥልጣናት ለጌሞች አዳዲስ የስያሜ መብቶችን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሮ ነበር።

ይህም ቴንሴንትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የጌም አምራች በመሆነው የአገሪቱ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ከባድ ጫናን ያሳደረው ይህ ውሳኔ፣ የቻይና ባለሥልጣናት የጌም ዘርፉ ላይ እየወሰዱ ያለው ሰፊ እርምጃ አካል ነው።

መረጃ አቅራቢ ከሆነው ሲኤንጂ በተባለ ኩባንያ ጋር በትብብር የወጣው ሪፖርት በድመዳሜው 75 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊዎች ጌም ላይ የሚያጠፉት ጊዜ በሳምንት ከሦስት ሰዓታት ያነሰ ነው ብሏል።

ቴንሴንትን ጨምሮ የቻይና የጌም አምራቾች “አመርቂ” ውጤት አስመዝግበዋልም ብለሏል - ሪፖርቱ።

የእስያ የጌም ገበያ ባለሙያ የሆኑት ኒኮ ፓርትነርስ ሪፖርቱ በቻይና የጌም ገቢ እየቀነሰ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል።

ሆኖም የኒኮ ፓርትነርስ መሥራች ሊዛ ኮስማስ መጪው ጊዜ አዎንታዊ ይመስላል ብለዋል። ኤሌክትሮኒክስ ስፖርት፣ የኮምፒውተር ጌም እና መሰል ጨዋታዎች ከ700 ሚሊዮን በላይ የጌም ተጫዋቾች በኢኮኖሚው ጥሩ እንቅስቃሴ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ጨምረውም አዳዲስ ጌሞች መፈቀድ ሲጀምሩ እና በታችኛው አስተዳደር ደረጃ የቁጥጥር ማስተካከያ ሲደረግ ከዚህም የተሻለ መልካም ውጤት እንገኛለን ብለዋል።

የቻይና መንግሥት በአገሪቱ እየጨመረ ለመጣው የዐይን ችግር፣ ትኩረት ማጣት፣ የአእምሮ ጤና እክል እና የእንቅልፍ መዛባት የቪዲዮ ጌም ሱሰኝነትን ተጠያቂ ያደርጋል።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለተጣለው የእንቅስቃሴ ገድብ ምክንያት የትምህርት አሰጣጡ ኢንተርኔትን መሠረተ ያደረገ መሆኑ ስጋትን ጨምሮ እንደነበር ተጠቅሷል።

በጌም ዘርፉ ላይ ከተደረገው ቁጥጥር በኋላ ለቻይና የተሰራው እና የቲክቶክ አቻ የሆነው ዶይን የተባለው ማኅበራዊ ሚዲያን ከ14 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት በቀን ከ40 ደቂቃ ለዘለለ ጊዜ እንዳያዩ ታግደዋል።

ሆኖም በአገሪቱ ክረምት በመቃረቡ እና የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ ህጻናት በቤት ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ ከፍ እያለ ነው። በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማዝናናት በራሳቸው የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንት ልጆች እንዲጠቀሙ እያደረደረጉ እንደሆንም ይነገራል።

ጌሞች አሁን በቻይና አዋቂ ሰዎች ዘንድም ያለው ተወዳጅነታቸው እየጨመረ እንደሆንም ጠቅሷል። በዚህ ሳምንት ቻይና ዴሊይ ያወጣው ሪፖርት ደግሞ በቤት ውስጥ የሚውሉ አረጋውያን “ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር” የበይነ መረብ ጌም መጫወት መጀመራቸውን አስነብቧል።