አሜሪካ ሁዋዌ እና ዜድቲኢን ጨምሮ በአምስት የቻይና ኩባንያዎች ላይ እገዳ ጣለች

ታትሟል

አሜሪካ በብሔራዊ ደኅንነቷ ላይ አለ ካለችው ስጋት ጋር በተያያዘ ከአምስት ታላላቅ የቻይና ታዋቂ ኩባንያዎች ጋር ምንም አይነት ሽያጭ እና ግዢ እንዳይካሄድ እገዳ ጣለች።

ይህ እገዳ ግዙፎቹን የኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ የሆኑትን ሁዋዌ እና ዜድቲኢን ጨምሮ በአምስት የቻይና ተቋማት ላይ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ በደኅንነት ስጋት ምክንያት አዳዲስ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ቁሳቁሶች ወደ አገሯ እንዳይገቡ እና እንዳይሸጡ ታዟል።

ሌሎቹ ስማቸው የተጠቀሰው እገዳው የተጣለባቸው የቻይና ኩባንያዎች ሂክቪዥን፣ ዳሁዋ እና ሃይቴራ የተባሉ ሲሆኑ፣ የቪዲዮ የደኅንነት መቆጣጠሪያዎች እና ባለሁለት ሞገድ የሬዲዮ ግንኙነት መሳሪያዎች አምራች ተቋማት ናቸው።

እንዲህ አይነቱ እርምጃ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በአሜሪካ ተቆጣጣሪ ተቋማት አማካይነት ሲወሰድ የመጀመሪያው ነው።

ውሳኔውን ተከትሎ ሂክቪዥን በሰጠው ምላሽ ምርቶቹ በአሜሪካ ደኅንነት ላይ ምንም አይነት ስጋትን አይደቅኑም ብሏል።

ጨምሮም የእገዳ ውሳኔው “የአሜሪካንን ብሔራዊ ደኅንነት በመጠበቅ በኩል የሚያበረክተው ነገር የለም። ይልቁንም የአሜሪካ ትናንሽ የንግድ ተቋማት፣ የአካባቢ ባለሥልጣናት፣ ትምህርት ቤቶችን እና ግለሰብ ተጠቃሚዎች እራሳቸውን፣ ቤታቸውን፣ የሥራ ቦታቸውን እና ንብረታቸውን ለመጠበቅ የሚያወጡትን ወጪ ከፍ በማድረግ ይጎዳቸዋል” ብሏል።

ሁዋዌ እና ሌሎች ኩባንያዎች ለቻይና መንግሥት መረጃ ያቀብላሉ በሚል የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

የአሜሪካ ፌደራል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኮሚሽን እንዳለው፣ ይህ በቻይና ኩባንያዎች ላይ የተጣለው እገዳ በአባላቱ በሙሉ ድምጽ ተቀባይነት አግኝቷል።

“ኮሚሽኑ አስተማማኝ ያልሆኑ የኮሚዩኒኬሽን መሳሪያዎች ፈቃድ አግኝተው ወደ አሜሪካ ገብተው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በማድረግ ብሔራዊ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ነው” ሲሉ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ጄሲካ ሮሰንዊረቼል ባወጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።

ጨምረውም “አዲሱ ትዕዛዝ በቴሌኮሚዩኒኬሽን አማካይነት ሊያጋጥሙ ከሚችሉ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶች የአሜሪካንን ሕዝብ ለመጠበቅ እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች ዋነኛው አካል ነው” ብለዋል።

አሁን በቻይና ኩባንያዎች ላይ የተጣለው ዕገዳ ወደ ኋላ ሄዶ ተግባራዊ ስለማይደረግ፣ የተጠቀሱት ተቋማት ቀደም ሲል ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ፈቃድ ያገኙ እቃዎች እንዲሸጡ ተፈቅዶላቸዋል።

ነገር ግን ቀደም ሲል ወደ አገሪቱ እንዲገቡ እና እንዲሸጡ የተፈቀዱትን መሳሪያዎች በተመለከ ያለውን ውሳኔ መልሶ ለማየት ኮሚሽኑ አስተያየት እየጠየቀ ሲሆን፣ በዚህም የተሰጠው ፈቃድ ሊሰረዝ የሚችልበት ዕድል አለ ማለት ነው።  

በቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ የተጣለው ይህ እገዳ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳሰባቸው ካለው የስለላ ስጋት ጋር የተያያዘ ነው።

በቻይና ቴሌኮም ኩባንያዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እና በአሜሪካ ገበያ ውስጥ ያለቸውን እንቅስቃሴ የመገደብ እርምጃ የተጀመረው በባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን ነበር።

በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራም አመራር ጊዜ ደግሞ ቁጥጥሩ የበለጠ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ እርምጃው በወቅቱ ፕሬዝዳንት ባይደንም ተግባራዊ እየሆነ ነው።