ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአፍሪካ በሕፃናት መጫወቻዎች ውስጥ እየተደበቁ ወደ ቻይና የሚወሰዱ የተፈጥሮ ሀብቶች
ኬፕ ታውን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያሉ የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች የሕፃናት መጫወቻ የሚል የካርቶን ሳጥን ወደ ቻይና ሊጫን መሆኑን ሲመለከቱ ጥርጣሬ ገባቸው።
ቻይና መጫወቻ ለመላው ዓለም በማከፋፈል እንጂ ወደ አገሯ በማስገባት አይደለም የምትታወቀው።
ሳጥኖቹ ለምርመራ እንዲከፈቱ ተደረገ። በሕፃናት መጫወቻ ፈንታ ዝርያቸው በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋት በሽንት ቤት ወረቀት ተጠቅልለው ተገኙ።
በጠቅላላው 23 ሺህ የሚሆን ኮኖፓይተም የተባለው ብርቅዬ ችግኝ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ሚያዝያ 2022 ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።
ተቆጣጣሪዎች ከወራት በፊት አንድ ዕቃ አጓጓዥ ድርጅት እንዲሁ ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅሞ ዕፅዋት ሊያግዝ ሲሞክር በቁጥጥር ሥር በመዋሉ ነው በተጠንቀቅ ሲጠብቁ የቆዩት።
ከአንድ ዓመት በኋላ በተመሳሳይ አየር ማረፊያ እንጉዳይ የሚል ፅሑፍ የተለጠፈባቸው ካርቶኖች ተደርድረው ታዩ። ይህም ዕቃ መዳረሻው ቻይና ነው።
ሳጥኖቹ ሲከፈቱ ውስጣቸው ያለው እንጉዳይ ሳይሆን 12 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ብርቅዬ ዕፅዋት ናቸው።
ከመርማሪ ፖሊሶቹ መካከል አንዱ “ይህ ዝውውር የሚቆም አይመስለም” ይላሉ። “አንዱን የሕገ-ወጥ ዝውውር መላ ስንደርስበት ሌላ መንገድ ይዘው ብቅ ይላሉ።”
ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ከ650 በላይ ዝርያ ያላቸው 1 ሚሊዮን ገደማ ብርቅዬ ዕፅዋት በሕገ-ወጥ መንገድ ሊዘዋወሩ ሲሰናዱ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ፅዕዋቱ በደቡባዊ አፍሪካ አገራት አድርገው ወደ ሌሎች ክፍለ ዓለማት ሊጋዙ ሲሉ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ትራፊክ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ይገልጿል።
ድርጅቱ እንደሚለው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብቻ በየሳምንቱ ከሦስት ሺህ በላይ በሕገ-ወጥ የሚዘዋወሩ ዕፅዋት በቁጥጥር ሥር ይውላሉ።
እኒህ ብርቅዬ ዕፅዋት በተለይ በምሥራቅ እስያ አገራት ዘንድ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከጥቅጥቅ ጫካዎች እያወጡ ማቅረብ ጀምረዋል የሚለው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ የብዝኃ-ሕይወት ተቋም ነው።
በዚህ ምክንያት ሰኩለንት ካሩ የተሰኘው በደቡብ አፍሪካ እና በናሚቢያ የሚገኘው እጅግ ሰፊ ቦታ የሚሸፍን የተፈጥሯዊ ይዞታ ብዝኃ-ሕይወት አደጋ ላይ እየወደቀ ይገኛል።
የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅቶች እንደሚሉት በዚህ ሥፍራ 6 ሺህ ዓይነት ሰኩለንት የተሰኙ ዕፅዋት ሲገኙ፣ 40 በመቶው ሌላ ቦታ የማይገኙ ናቸው።
በጣም ከሚታወቁ ሰኩለንት ዕፅዋት መካከል ብዙውን ጊዜ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚዘዋወረው ኮኖፓይተም የተሰኘው ሲሆን፣ የዚህ ዝርያ ቅጥያዎች ለገበያ እንዳይውሉ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል።
እኒህ ዕፀዋት ብርቅዬ እና ሊጠፉ የተቃረቡ በመሆናቸው ምክንያት ነው ለገበያ እንዳይቀርቡ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ የተጣለው።
የተፈጥሮ ጥበቃ ባለሙያዎች እንደሚሉት እንደዚህ ያሉ በመጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ዕፀዋትን ለማዘዋወር ቀላል ስለሆኑ በፖስታ እና በዕቃ ጫኞች ምክንያት ከአገር አገር ይጓጓዛሉ።
ዓለም አቀፉ የገቢዎች ድርጅት [ደብሊውሲኦ] በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚጠቁመው ብዙውን ጊዜ መሰል ዕፅዋት የሚዘዋወሩት በትናንሽ ጥቅሎች ሲሆን፣ በ2022 ከተያዙት መካከል 43 በመቶው በፖስታ ሲዘዋወሩ ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት። ይህ ቁጥር ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
“ወንጀለኞች በርካታ ዘዴዎችን ተጠቅመው እኒህን ዕፅዋት በፖስታ ይልካሉ። አብዛኛውን ጊዜ የሚደበቁት በሕፃናት መጫወቻ ውስጥ ነው” ይላሉ የዓለም አቀፉ የፖስት አገልግሎት ማኅበር የደኅንነት ባለሙያ ዶውን ዊልክስ።
ባለሙያዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አብዛኞቹ ጥቅሎች የሚመጡት ከአፍሪካ አሊያም ከእስያ ነው።
ባለፈው መጋቢት ደግሞ በሰሜን ምሥራቅ ቪዬትናሟ ሃይ ፎንግ የሚገኙ ባለሥልጣናት መነሻው ከናይጄሪያ የሆነ አጠራጣሪ ጥቅል አስተዋሉ።
መርማሪዎች ጠጋ ብለው ሲመለከቱ ሳጥኖቹ በጥቁር ቀንዶች የተሞሉ ናቸው። ነገር ግን በደንብ ሲመረምሩት ጥቁር ቀለም የተቀቡ የዝሆን ጥርሶች ሆነው ተገኝተዋል።
የተፈጥሮ ሀብቶች ሕገ-ወጥ ዝውውርን የሚቆጣጠሩ ባመሉያዎች የዝሆን ጥርስ ቀለም ተቀብቶ ሲዘዋወር ተመልክተው እንደማይውቁ ይናገራሉ። አብዛኛውን ጊዜ የዝሆን ጥርስ በቪዬትናም በኩል የሚዘዋወረው በከብቶች ቀንድ ውስጥ ተደብቆ ነው።
ሃይ ፎንግ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የዝሆን ጥርሶች በቁጥር 550 ሲሆኑ ክብደታቸው 1600 ኪሎ ግራም አካባቢ ነው። ከሕገ-ወጥ ዝውውሩ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሁለት ሰዎች ናይጄሪያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርገዋል።
የዝሆን ጥርስ ሕገ-ወጥ ዝውውር ጉዳት እያደረሰባቸው ያሉ የአፍሪካ አገራት አንጎላ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ናቸው። ባለፉት 30 የዓመታት የአፍሪካ ዝሆኖች ቁጥር 90 በመቶ ቀንሷል።
የአፍሪካ የዱር ዝሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመጥፋት ላይ ያለ ተብሎ የተመዘገበ ነው።
ዝሆኖች ብቻ ሳይሆኑ በአፍሪካ ጠረፎች የሚገኙ ሻርኮችንም መጠበቅ እጅግ አዳጋች እየሆነ መጥቷል። በተለይ ደግሞ ለሻርክ ሾርባ የሚፈለገው ክንፉ በበርካታ አገራት በውድ ዋጋ የሚሸጥ ነው።
ከ500 በላይ የተመዘገቡ የሻርክ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን፣ አብዛኞቹ አሁንም ያለምንም የሕግ ገደብ ለገበያ ይቀርባሉ። ነገር ግን 60 የሚሆኑ የሻርክ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ስለተደቀነባቸው መሸጥም ሆነ መግዛት ተከልክሏል።
የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ጥበቃ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ይህንን ተጠቅመው ነው የሚያዘዋውሩት። ለምሳሌ በቅርቡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሻርክ ክንፍ በቁጥጥር ሥር ሲውል ግማሹ ሕገ-ወጥ የተቀረው ደግሞ ሕጋዊ ሆኖ ተገኝቷል።
ሕገ-ወጥ ዝውውሩ በጣም ውስብስብ እየሆነ አዳዲስ መንገዶች እየተጠቀመ ቢመጣም በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ዝውውሮችም ከዓመት ዓመት እየጨመሩ ናቸው።