ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሚሊዮኖች ብርቅዬ የተባለውን ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ ተመለከቱ
በመላው ሜክሲኮ፣ አሜሪካ እና ካናዳ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽን ተመለከቱ።
ብርቅዬ በተባለለት አጋጣሚ ጨረቃ በምድር እና በፀሐይ መካከል ስትንቀሳቀስ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ በመፍጠር ጨለማ ፈጥራለች።
በሜክሲኮ የባህር ዳርቻ የጀመረው የፀሐይ ግርዶሽ በኒያግራ ፏፏቴ አቋርጦ በካናዳ የባህር ዳርቻ ተጠናቋል።
ግርዶሹ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በሜክሲኮ ማዛትላን አካባቢ ነው።
መጀመሪያ ላይ ጨረቃ ፀሐይን ጠርዝ የነካች መስሎ ነበር። ቀስ በቀስም ሙሉ ለሙሉ ጸሐይን በመጋረድ ጨለማ ሲፈጠር ሚሊዮኖች በደስታ ተከታትለውታል።
የ11 ዓመቷ የዳላስ ቴክሳስ ነዋሪዋ አዲ ዋልተን-ኪንግ ሂደቱ አዝጋሚ ነበር ብላለች።
"ምንም የጥርስ ምልክት ሳታወጣ ጨረቃ ፀሐይን እየበላች ይመስል ነበር" ስትል ሂደቱን ገልጻለች።
"እንዲህ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር። በጣም ጨለማ ነበር:: ልክ እንደ ምሽት ጨለማ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር። ነገር ግን ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ነበር።"
የሙቀት መጠኑ በፍጥነት ከመውረዱም በላይ እንደተማረችውም እንስሳት ጸጥ አሉ።
"በኋላም ቀስ በቀስ ብርሃን መታየት ጀመረ። ወፎቹም መዘመር ጀመሩ። በጣም አስገራሚ ነበር። ማለቁ አዝኛለሁ" ብላለች።
አንዳንዶችም አጋጣሚውን ተጠቅመው ታሪካዊ ቀን አድርገውታል። በመቶዎች የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ጎዳናዎች ላይ የጅምላ ሠርጋቸውን አከናውነዋል።
ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ 300 ጥንዶች በራሰልቪል አርካንሳስ ምድር ከጸሐይ ከመጋረዷ ሰከንዶች በፊት ጋብቻቸውን ፈጽመዋል።
ምድር በድጋሚ የጸሐይ ብርሃን ስታገኝ ኬኮች ተቆርጠው ቶታል ኤክሊፕስ ኦፍ ኸርት ፌስቲቫል የተባለው የጅምላ ጋብቻ በዳንስ ደምቋል።
አማተር የስነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ዳርሲ ሃዋርድ ከዛሬ በፊት ብዙ ግርዶሽ አይታለች። "ሁሉም የራሱ አሻራ አለው" ብለዋል።
በአባታቸው ምክንያት ወደ ኮስሞስ የተሳቡት የ 70 ዓመቷ አዛውንት "በቴሌስኮፕ ጁፒተርን አያለሁ... ሳተርን ማየት ችያለሁ። ያንን በህዋ ላይ ሳየው ሁሉም ነገር በዓለም ላይ ትክክል እንደሆነ አውቃለሁ" ብለዋል።
በክሊቭላንድ እኩለ ቀን ላይ ኮከቦች መታየታቸውን ተከትሎ የበዓል ዋዜማ ይመስል በደስታ ርችቶች ሲተኮሱ ነበር።
ብዙ ትላልቅ የአሜሪካ ከተሞች ሙሉ የጸሐይ ግርዶሽ ለማየት አልታደሉም። ኒውዮርክ ማንሃታን በሚገኘው ሰማይ ጠቀሱ ኤጅ ህንጻ ላይ ብርካቶች ከፊል ግርዶሹን ለመመልከት ችለዋል።
ፀሐይ የጨረቃ ቅርጽ የያዘችበት እና ከተማዋ በብርሃን ፍንጣቂ ሰትሞላ ለማየትም ታድለዋል።
ግርዶሹ ከአሜሪካ ወደ ካናዳ በሚያቋርጥበት የኒያጋራ ፏፏቴ ቱሪስቶች የሁለቱም አገራት የድንበር አካባቢዎችን አጨናንቀው ነበር።
እዚህ ግን አየሩ ከባድ ፈተና ደቅኖ ነበር። ጥቅጥቅ ያለው ደመና በአብዛናው ሰማዩን ከዕይታ ጋርዶታል።
ሙሉው ግርዶሽ ሲፈጠር ግን ደመናው መከፈቱ ለብዙዎች ደስታን ፈጥሯል።
ቀትሎ ወደ ደቂቃዎች ጨለማ የተዋጠችው ሞንትሪያል ነበረች።
በሞንትሪያል፣ 20 ሺህ ሰዎች በማክጊል ዩኒቨርሲቲ ግቢ በሚገኝ ሜዳ ላይ ተሰባስበው አጋጣሚውን ተከታትለዋል። የትሮቲየር ጠፈር ኢንስቲትዩትም ዝግጅት ነበረው።
የፕሮግራሙ ኃላፊ ካሮይና ክሩዝ-ቪናቺያ “8 ሺህ ሰዎችን ጠብቅን ነበር” ብላለች። የአየሩ ሁኔታ ፍጹም ግልጽ እና ብሩህ ሰማይ ነበር። ሕዝቡ በጣም ደስተኛ ነበር ብላለች።
ሙሉ ግርዶሽ ማየት ከሚችሉት የመጨረሻ አካባቢዎች አንዷ በሆነችው በኒውፋውንድላንድ ፎጎ ጥቂት ሰዎች ብቻ የጸሐይ ግርዶሹን ለመመልከት ወጥተዋል።
ዳላስ የምትገኘው አዲ ዋልተን-ኪንግ ከወዲሁ ዕቅድ እያወጣች ነው።
ቴክሳስ ተመሳሳይ ክስተት ለማየት 300 ዓመታት ለመጠበቅ ትገደዳለች። ስለዚህ በ2044 ለሚኖረው ለቀጣዩ ግርዶሽ ወደ ሰሜን አሜሪካ መጓዝ ይኖርባታል።
ያኔ ደግሞ እሷ በጠቅላላ ግርዶሽ ዙሪያ የበለጠ ዕውቀት ይኖራታል። "በዚያ ጊዜ ሳይንቲስት መሆን እፈልጋለሁ" ብላለች።