ኤሎን መስክ ከቴስላ ድርሻው 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን ለእርዳታ ድርጅት ሰጠ

ታትሟል

የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነው ኤሎን መስክ ባለፈው ዓመት 1.9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የቴስላ ድርሻውን ለእርዳታ ድርጅት መስጠቱን አስታወቀ።

መስክ 11.6 ሚሊዮን የቴስላ ሼር ለእርዳታ ድርጅት መስጠቱ የታወቀው የባለቤትነት ዝውውር መዝገብ ላይ ከሰፈረ በኋላ ነው።

መስክ ካለው የባለቤትነት ድርሻው ውስጥ ለእርዳታ ድርጅት አሳልፎ እንደሰጠ እንጂ ለየትኛው እንደሆነ ግን በመዝገቡ ላይ አልተጠቀሰም።

ለአሜሪካ ሴኪዩሪቲ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን ገቢ የተደረገው ሰነድ፣ መስክ የቴስላ ድርሻውን አሳልፎ የሰጠው ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ነሐሴ እና ኅዳር ወር መካከል መሆኑን አሳይቷል።

ቴስላ ጉዳዩን በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

መስክ ከቴስላ ድርሻው የተወሰነውን ለእርዳታ ድርጅት ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እአአ 2021 ላይ 5.74 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ድርሻውን ለእርዳታ ድርጅት አሳልፎ ሰጥቶ ነበር።

መስክ በዚህ ዓመት በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ በምትገኘውና ካሜሩን ተብላ በምትጠራው አውራጃ ለሚገኙ ትምህር ቤቶች እና ብራወንስቫይል ከተማ 20 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ማቀዱን ተናግሮ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መስክ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. በዓመቱ መጨረሻ ላይ ከትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሥራውን ሌላ ሰው ሊረከበው እንደሚችል ጠቁሟል።

“ስገምት በዚህ ዓመት መጨረሻ (እአአ 2023) ኩባንያውን የሚመራ ሌላ ሰው ማፈላለጉ የተሻለ ይመስለኛል” ብሏል በትዊተር ገጹ።

መስክ ከትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚለቀው ኩባንያውን ለማረጋጋት እና በፋይናንስ ጤናማ ለማድረግ ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት መሆኑን ገልጿል።

መስክ አዲስ ሥራ አስኪያጅ የመሾም ሃሳብን ያስተዋወቀው በርካታ ሰዎች ከቴስላ ይልቅ ሙሉ ትኩረቱን ትዊተር ላይ አድርጓል ብለው እየተቹት ባለበት ወቅት ነው።

መስክ በቡድን 20 (ጂ20) የመሪዎች ስብሰባ ላይ በትዊተር፣ ቴስላ እና በስፔስኤክስ ያለውን ኃላፊነት ለመወጣት በውጥረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግሮ ነበር።

መስክ ከወራት በፊት ግዙፉን ማኅበራዊ ሚዲያ በ44 ቢሊዮን ዶላር መግዛቱ ይታወሳል። መስክ ትዊተርን ከገዛ በኋላ ኩባንያው የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ለመግባት ታቀርቦ እንደነበረ ተናግሯል።

“ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሥራ ጫናዬ በጣም ጨምሯል” ያለው መስክ፤ “በጣም ብዙ ሥራ አለኝ፤ ይሄ እርግጥ ነው” ብሎ ነበር ኢንዶኔዢያ ባሊ ላይ በነበረው ስብሰባ።