የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ቀጥታ ዜና እያሰራጨ እያለ ተጠልፎ እንደነበር ተገለጸ

ታትሟል

የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ቅዳሜ መስከረም 28፣ 2015 ዓ.ም የቀጥታ ዜና እያሰራጨ በነበረበት ወቅት ተጠልፎ እንደነበር ተገለጸ።

ዜናውም ተቋርጦ በሃገሪቱ መሪ ላይ የተነሳው ተቃውሞ መተላለፍ ጀመረ።

በስክሪኑ ላይ ጭንብል ከታየ በኋላ የኢራኑ ታላቁ መሪ አሊ ካሜኒ ምስል በእሳት ነበልባል ሲያዝ አሳይቷል።

ይህንን ያደረገው ቡድን ራሱን “አዳላት አሊ” ወይም “የአሊ ዳኛ” ይሰኛል።

በማህሳ አሚኒ ሞት ምክንያት ባገረሸው ተቃውሞ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ ሶስት ሰዎች በጥይት ከተገደሉ በኋላም የቴሌቪዥን ጣቢያው መጠለፉ ተገልጿል።

ማህሳ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በቴህራን የደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ውላለች።

 የ22 ዓመቷ ኢራናዊት ኩርድ በቁጥጥር ስር ከዋለች ከሶስት ቀናት በኋላ በእስር ላይ እያለች ህይወቷ አልፏል።

ሞቷም በመላ ሃገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞ ማዕበል ቀስቅሷል።

ቅዳሜ በሃገሬው ሰዓት አቆጣጠር 12 ሰዓት ላይ ይተላለፍ የነበረ ዜና ተቋርጦ የኢራኑ ታላቁ መሪ ጭንቅላታቸው ኢላማ ተደርጎበት፣ የማህሳና በቅርብ በነበረው ተቃውሞ የተገደሉ ሶስት ሴቶችንም ምስሎች አስተላልፏል።

በፎቶው ላይ ከተላለፉ መልዕክቶች አንዱ “ተቀላቀሉን እና ተነሱ” የሚሉ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “የወጣቶቻችን ደም ከመዳፋችሁ ላይ ይንጠባጠባል” ይላል።

ጠለፋውም ለጥቂት ሰኮንዶች ብቻ ነው የቆየው ተብሏል።

እንዲህ አይነቱ በአያቶላ አሊ ካሜኒ ላይ የአመፅ ማሳያዎች በኢራን ታሪክ ውስጥ የተለመዱ አይደሉም። ታላቁ መሪ በኢራን ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ናቸው። ነገር ግን በቅርቡ የማህሳን ሞት ተከትሎ በግልጽ ተቃውሞዎች መታየት ጀምረዋል ።

በተጨማሪም ቅዳሜ እለት በቴህራን ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሴት ተማሪዎች “ከዚህ አካባቢ ይጥፉ” እያሉ መፈክር ሲያሰሙ እንደነበር የማህበራዊ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።

በኢራን ተቃውሞ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ150 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የመብት ተሟጋቾች ድርጅቶች ተናግረዋል።