ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል የጋዛ-ግብጽ ድንበር መተላለፊያን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯን ገለጸች
የእስራኤል ጦር በጋዛ እና ግብጽ ድንበር ላይ የሚገኘውን እና ፊላዴልፊ ኮሪደር [መተላለፊያ] ተብሎ የሚጠራውን ስትራቴጂካዊ ቀጠና መቆጣጠሯን አስታወቀች።
ሐማስ ወደ ጋዛ የጦር መሳሪያ ለማስገባት የሚጠቀምባቸው 20 የሚጠጉ ዋሻዎች መገኘታቸውን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የግብጽ ቴሌቭዥን ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው እስራኤል ይህንን ያለችው በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ራፋህ ከተማ የምታካሂደውን ጥቃት ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው ብሏል።
እስራኤል ይህንን የገለጸችው ከግብጽ ጋር ከፍተኛ ውጥረት በገባችበት ወቅት ነው።
"ባለፉት ቀናት የእስራኤል ወታደሮች በግብጽ እና ራፋህ ድንበር ላይ የሚገኘውን የፊላዴልፊ ኮሪደር ተቆጣጥረዋል" ሲሉ የመከላከያ ሠራዊቱ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።
መተላለፊያው ለሐማስ "የህይወት መስመር" ነው ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም ቡድኑ "በጋዛ ሰርጥ የጦር መሳሪያዎችን ያስገባ ነበር" ብለዋል።
ጦሩ በአካባቢው የተገኙትን ዋሻዎች "እየመረመሩ.. እና እያጸዱ" ነው ብለዋል።
ሃጋሪ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሁሉም ዋሻዎች ወደ ግብጽ ስለመሻገራቸው እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ተናግረዋል ሲል ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
የፊላዴልፊ መተላለፊያ ከግብጽ ጋር የሚያዋስንና 100 ሜትር ስፋት እና 13 ኪሎሜትር እርዝማኔ ያለው ነው
ግብጽ ከዚህ ቀደም ማንኛውንም የጦር መሣሪያ ዝውውር ለመቆጣጠር የድንበር ተሻጋሪ ዋሻዎችን ማውደሟን ተናግራለች።
“ከፍተኛ” የግብጽ ምንጭን ጠቅሶ አልቃሂራ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ እስራኤል "እነዚህን ክሶች የምታቀርበው በፍልስጤማውያኑ ራፋህ ከተማ ላይ የምታካሄደውን ጥቃት ለመቀጠል እና ጦርነቱን ለፖለቲካዊ ዓላማ ለማራዘም ሲሉ" ሲሉ ከሰዋል።
ሐማስ መስከረም 26 ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ጦርነቱን ለማሸነፍ ራፋህን መቆጣጠር እንዳለባት አጥብቃ ትናገራለች።
ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ 36,170 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚያካሂደውን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ ከሦስት ሳምንታት በፊት የራፋህን መሻገሪያን ከተቆጣጠረ ወዲህ በግብጽ እና በእስራኤል መካከል ያለው ውጥረት ተባብሷል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በራፋህ አቅራቢያ በሚገኘው የድንበር አካባቢ አንድ የግብጽ ወታደር ተገድሏል።
ግብጽ የፍልስጤማውያን ጠንካራ ደጋፊ ስትሆን እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ እና እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ዜጎችን መግደሏን አውግዛለች።
እንደ እስራኤል ሁሉ ሐማስ ስልጣን ከያዘበት እአአ ከ2006 ጀምሮ ግብጽ ከጋዛ ጋር በሚያዋስናትን ድንበር ዘግታ ኖራለች። ሐማስ በግብጽ አሸባሪ የተባለው የእስላማዊ ሙስሊም ወንድማማች አባል ነው።
ሆኖም ግብጽ ከሃማስ ጋር ያላትን ግንኙነት በመጠበቅ በእስራኤል እና በቡድኑ መካከል በተዘዋዋሪ በሚደረጉ ንግግሮች ላይ እንደ አሸማጋይ በመሆን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ እና በሐማስ የተያዙ የእስራኤል ታጋቾችን ለማስፈታት ስትሞክር ቆይታለች።