አማዞን፣ ሒልተን እና ፔፕሲ በአውሮፓ የሚገኙ ስደተኞችን ለመቅጠር ቃል ገቡ

የዩክሬን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አማዞን፣ ሒልተን እና ፔፕሲ ከተለያዩ አገራት ተፈናቅለው ወደ አውሮፓ የገቡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመቅጠር ቃል ገቡ።

አማዞን በአገራቸው ጦርነትንና ሌሎች ችግሮችን ፈርተው የተሰደዱ ስደተኞችን ለመርዳት በሚያደርገው እንቅስቃሴ 5 ሺህ ዩክሬናውያንን እንዲሁም ከሌሎች አገራት የመጡ ስደተኞችን እንደሚቀጥር አስታውቋል።

ከ40 በላይ ትልልቅ የአውሮፓ ኩባንያዎች 250 ሺህ ዩክሬናውያን ዜጎች እና ከሌሎች አገራት የመጡ ስደተኞችን እንቀጥራለን ብለዋል።

የሒልተን ሆቴል ቅርንጫፎች፣ አዴኮ እና ማይክሮሶፍት የመሳሰሉ ድርጅቶች የስራ ወይም የሙያ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ከገቡ ድርጅቶች መካከል ይገኙበታል።

በአለም ላይ የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በግዳጅ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 110 ሚሊዮን ደርሷል።

በርካታዎቹ ስደተኞች ስራ ማግኘት ፈታኝ እንደሆነባቸው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ማርጋሪቲስ ሺናስ ይናገራሉ።

“ይህ በአውሮፓ ታይቶ የማያውቅ የኩባንያዎች ድጋፍ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ኑሯቸውን እንዲያቋቁሙ እንዲሁም በዩክሬን ውስጥ የሚወዷቸውን ቤተሰቦችና ዘመዶች ለመደገፍ ያስችላቸዋል” ብለዋል።

ሩሲያ በዩክሬን የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በአውሮፓ የሚኖሩ የዩክሬን ስደተኞች ቁጥር ከ5.9 ሚሊዮን በላይ ሆኗል ከነዚህም ውስጥ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑት በሩሲያ እና ቤላሩስ ነው የሚገኙት።

ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች እንደ ሶሪያ፣ ሱዳን እና አፍጋኒስታን በተከሰቱ ጦርነቶች ህይወታቸውን ለማቆየት ስደትን መርጠዋል።

ስደተኞች ስራ እንዲያገኙ የተጀመረውን ጥረት የሚያስተባብረው ቴንት ፓርትነርሺፕ ፎር ሪፉጂስ የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት ነው።

በድርጅቱ መሰረት በአውሮፓ ከሚገኙት አብዛኞቹ የዩክሬን ስደተኞች ሴቶች መሆናቸውን እና ስራ በማግኘቱ ረገድም የተለያዩ እንቅፋቶች ያጋጥማቸዋል ብሏል።

ከነዚህም ውስጥ የተሰደዱበትን አገር ቋንቋ አቀላጥፎ አለመናገር እንዲሁም የህጻናት እንክብካቤ ኃላፊነት ፈታኝ አድርጎባቸዋል።

በዚህም ድርጅት አነሳሽነት አማዞን፣ ሂልተንና እና ማሪዮትን ጨምሮ ትልልቅ ኩባንያዎች 13 ሺህ 680 ዩክሬናውያንን እና ሌሎች ስደተኞችን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ለመቅጠር ቃል ገብተዋል።

በተጨማሪም እንደ አዴኮ ያሉ የቅጥር ኤጀንሲዎች 150 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞችን ስራ ለማስያዝ እርዳታ አደርጋለሁ ብሏል።

በተጨማሪም አክሰንቸር እና ማይክሮሶፍት ያሉ ድርጅቶች ከ86 ሺህ በላይ ስደተኞችን በስልጠና እንደሚያግዙ አስታውቀዋል።