ፕሬዚዳንት ባይደን በንግስቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ለንደን ገቡ  

ታትሟል

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፊታችን ሰኞ መስከረም 9፣ 2015 ዓ.ም በሚካሄደው የዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ለንደን ገቡ።

ፐሬዚዳንት ባይደን 500 ያህል የሚጠጉ የሃገር መሪዎች እና ተወካዮች ለአስርት ዓመታት ባልታየ ሁኔታ በሚሰባሰቡበት ስን ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው ወደ ለንደን ያቀኑት። 

የካናዳ፣ የአውስትራሊያ እና የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንግሊዝ ቀድም ብለው ገብተዋል።

የሳዑዲ አረቢያውን አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጨምሮ አንዳንድ እንግዶች መጋበዛቸው ውዝግብ ተፈጥሯል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔሴ፣ የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደር፣ የባንግላዲሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲና፣ የሲሪላንካው ፕሬዝዳንት ራኒል ዊክሪሜሲንግን ጨምሮ ሌሎች የኮመንዌልዝ መሪዎች በስነ ስርዓቱ ላይ እንደሚገኙ ይጠበቃል። ህንድ በፕሬዚዳንት ድሮፓዲ ሙርሙ ትወከላለች።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ አይሪሹ ሚሼል ማርቲን፣ የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየር እና የጣሊያኑ ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላም በንግሥቲቱ ቀብር ላይ ይገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት የዓለም መሪዎች መካከል ናቸው።

ከመላው አውሮፓ የንጉሣዊያን ቤተሰብ አባላትም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ብዙዎቹ እንግዶች በዌስት ሚኒስትር አዳራሽ በመገኘት ለንግስቲቱ ሸኝት የሚያደርጉ ሲሆን በላንካስተር ሃውስ ተገኝተው ሃዘናቸውን በጽሑፍ ያሰፍራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ትኩረት የተሰጠው ዛሬ በቤኪንግሃም ቤተመንግስት በንጉስ ቻርልስ ሦስተኛ የሚያስተናግዱት አቀባበል ይሆናል።

ለብዙ መሪዎች በጋራ ለመገናኘት እና በአንዳንድ ዲፕሎማሲዎች ጉዳይ ለመሳተፍ ብቸኛ ዕድላቸው ይሆናል።

በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙት እንግዶች መካከል አንዳንዶቹ  ግርምትን ፈጥረዋል።

የሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ግብዣ መደረጉ አነጋጋሪ ሆኗል።

እአአ በ2018 ቱርክ ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ፅህፈት ቤት ውስጥ የሳዑዲው ጋዜጠኛ ጀማል ኻውሾጊ እንዲገደል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ተብለው ይከሰሳሉ።  እሳቸውም ሆኑ መንግስታቸው ይህንን ያስተባብላሉ።

የኻውሾጊ እጮኛ ሃቲስ ጄንጊዝ እንዳሉት የአልጋ ወራሹ በዝግጅቱ ላይ እንዲገኙ መፍቀድ አልነበረበትም። ይህም በንግስቲቱ ማስታወሻ ላይ ጥቁር ጠባሳ የሚያኖር መሆኑን ተናግራለች።

በቻይና መንግሥት ላይ የሚሰነዘረውን የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች ክስ ተከትሎ  ለፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የተደረገው ግብዣ ሌላው ትችት ያስከተለ ጉዳይ ሆኗል።

በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ዢ አይገኙም። ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ኪሻን ወደ እንግሊዝ ይጓዛሉ።

የሩሲያ፣ የቤላሩስ፣ የማያንማር፣ የሶሪያ፣ የቬንዙዌላ እና የአፍጋኒስታን ተወካዮች አልተጋበዙም።

ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኒካራጓ ቢጋበዙም ከሃገር መሪዎች ይልቅ በአምባሳደሮች ብቻ ይወከላሉ።