ፖሊስ ሁለት የኢሕአፓ አባላት እና የፓርቲውን ጠበቃ "በሽብር ወንጀል" መጠርጠሩን ገለፀ

ይሳቅ ወልዳይ (ግራ)፣ አበበ አካሉ (መሃል) እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ (ቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, ZEMA/ABERA NIGUS

የምስሉ መግለጫ, ይሳቅ ወልዳይ (ግራ)፣ አበበ አካሉ (መሃል) እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ (ቀኝ)
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ባለፉት ቀናት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያ በፀጥታ ተቋማት እና በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ላይ "የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ተንቀሳቅሰዋል" ሲል ፖሊስ አመለከተ።

ተጠርጣሪዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፖለቲከኞች አበበ አካሉ እና ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ጠበቃ አበራ ንጉሥ ረቡዕ ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት መቅረባቸውን ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻ ላይ፣ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ተቋማት እና በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ላይ "የሽብር ጥቃት ለመፈፀም በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ በቀን 27/11/2018 ዓ.ም በጥብቅ ክትትል በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውለዋል" ብሏል።

ለዚህም ተግባራዊነት ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ አመራሮች ጋር "በድብቅ ግንኙነት በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ነበር" ብሏል።

ሁለቱ ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያው "በፌደራል ፖሊስ" አባላት የተያዙት ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም. በተለያየ ሰዓት እንደሆነ የቤተሰብ ምንጮች፣ ጠበቃ እና የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።

በቅድሚያ የተያዙት የኢሕአፓ ጠበቃ እንዲሁም ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጠበቃ በመሆኑ የሚታወቁት አበራ ንጉሥ ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ፖሊስ ከቤታቸው እንደያዛቸው አንድ የቤተሰባቸው አባል ተናግረዋል።

አቶ ይሳቅ ወልዳይ ቀን 8 ሰዓት ተኩል በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሌላኛው የኢሕአፓ አባል አቶ አበባ አካሉ ደግሞ አመሻሽ ላይ ከቤታቸው ውጭ በሆነ ስፍራ ምሽት ላይ መያዛቸውን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ሦስቱ ተጠርጣሪዎች "ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ በማሰብ" የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ተብለው ከተጠቀሱት ከህወሓት፣ "ፅምዶ" ተብሎ ከሚጠራው ኃይል እና በስም ያልተጠቀሱ ሌሎች "ፀረ-ሰላም ኃይሎች" ጋር ተቀናጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ፖሊስ አመልክቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ አባላትን በመመልመል እና በማደራጀት፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንቅስቃሴ በመሰለል ለፅምዶ ቡድን መረጃ በማቀበል መወንጀላቸውን ቢቢሲ የተመለከተው የፖሊስ ማመልከቻ ጠቅሷል።

በተጨማሪም "ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ" የፖለቲካ ክንፍ፣ የወታደራዊ አደረጃጀትና ሥልጠና ክንፍ፣ የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ክንፍ በማደራጀት ብልጽግና ፓርቲ "አገር የመምራት አቅም የለውም" በመሆኑም "በኃይልም ቢሆን ማስወገድ አለብን" በማለት ለተግባራዊነቱ እየሠሩ እንደነበረ ፖሊስ ወንጅሏቸዋል።

ለዚህም የትጥቅ ትግል የመጨረሻ አማራጭ መሆን እንዳለበት ውጭ አገር የሚገኙ ባላቸው ሦስት ሚዲያዎች ማለትም "አንከር፣ ኢትዮ-ፎረም እና ኢትዮ 360" ሚዲያዎች በኩል "የሐሰት-ፕሮፓጋንዳ በማሠራጨት ሕዝብ እና መንግሥትን ለማጋጨት እየሠሩ ይገኛሉ" ሲል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻው ላይ አስፍሯል።

በአሁኑ ወቅት በግለሰቦቹ ላይ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ የገለፀው ፖሊስ፣ ዛሬ ጠዋት በነበረው ችሎት ላይ ምርመራውን ለማጠናቀቅ የ14 ቀን ቀጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው መጠየቁን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ገልፀዋል።

ለዚህም ፖሊስ በምክንያትነት ያቀረበው፣ ሦስቱ ተጠርታሪዎች የተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ውስብስብ እና ለምርመራ ሰፊ ጊዜ የሚያስፈልገው ነው የሚል ነው። ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ከእስር ቢለቀቁ በምስክሮች ላይ የተለያየ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉም አመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ወንጀሉን እንዳልፈፀሙ በመግለፅ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የሆኑት ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ አበበ አካሉ፣ የልጆች አባት መሆናቸውን ጠቅሰው፥ "አገሬ ሰላም እንድትሆን እንጂ መንግሥት ላይ አመጽ አስነስቼ [አገሬ] እንድትበጠበጥ አልፈልግም" በማለት በፖሊስ የቀረበባቸውን ክስ እንደማይቀበሉ ለችሎቱ ማስረዳታቸውን አቶ ሰለሞን ገልፀዋል።

የኢሕአፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ይሳቅ ወልዳይም እንዲሁ፥ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆነው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ እና "በምርጫም ጭምር ስሳተፍ ነበር" በማለት የፖሊስን ውንጀላ ተቃውመዋል።

ጠበቆቻቸው በበኩላቸው፣ ሁለቱ የኢሐፓ አባላት እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ "በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ፣ ያደረጉትም ንግግር ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ያደረጉት ነው" በማለት የቀረበባቸው ውንጀላ "የሽብርን መስፈርት አያሟላም" ብለው መከራከራቸውን አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ፣ ለምርመራ ተጨማሪ 14 ቀን ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም በሚለው እና በዋስትና ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ዛሬ ረቡዕ ከሰዓት በድጋሚ ተሰይሞ ነበር።

ከሰዓት በነበረው ችሎት ላይ፣ ፖሊስ ጠረጠርኳቸው ያለበትን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ያደረጉትን "የሐሰት ፕሮፓጋንዳ" በተመለከተ የሽብር ይዘት አለው ወይስ የለውም የሚለውን ለመወሰን ተጠርጣሪዎቹ አደረጉት የተባለውን ንግግር ፖሊስ ነገ ሐሙስ እንዲያቀርብ አዝዟል።

ንግግሩን ተመልክቶ እና አድምጦ በፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ እና በዋስትና ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ችሎቱ ለዓርብ ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም ቀጥሯል።