ትግራይ ውስጥ ከባድ የጤና ስጋት የፈጠሩ 3 ተላላፊ በሽታዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትግራይ ክልል ወባ፣ ኮሌራ፣ የእብድ ውሻ በሽታ፣ እንዲሁም አባ ሠንጋ በወረርሽኝ መልክ መከሰታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።
የክልሉ ጤና ቢሮ እንደሚለው ከሆነ ከእነዚህ በሽታዎች መካከል ውስጥ ሶስቱ በከፍተኛ ደረጃ ስጋት ሆነዋል።
ቢሮው ለቢቢሲ በላከው መረጃ መሰረት የእብድ ውሻ በሽታ፣ አባ ሠንጋ እንዲሁም ወባ ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረ የመድሃኒት እጥረት፣ የጤና ተቋማት መዳከም እንዲሁም የመገናኛ መንገዶች መቋረጥና የአቅርቦት እጥረት ከተያያዥ ችግሮች ጋር ተደማምረው ለበሽታዎቹ መስፋፋት ዋና ምክንያቶች ሆነዋል።
ትግራይ ውስጥ የተከሰቱ ሶስት ከባድ የጤና ስጋቶች የትኞቹ ናቸው?
1. አባ ሠንጋ
አባ ሠንጋ ትግራይ ውስጥ ‘መገረም’ በሚል የሚታወቅ ሲሆን በቀላሉ ማወቅና ለጤና ባለሙያዎች ማሳወቅ ከሚቻሉ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው።
በዚህ ዓመት (2022) ማእከላዊ ዞን ናዕዴር ዓዴት ወረዳ ውስጥ 10 ሰዎች መያዛቸውን የሚያመላክት ሪፖርት ቀርቧል።
ከዚያ ወዲህ ወደ ክልሉ ጤና ቢሮ ሪፖርት የላኩ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በበሽታው የተጠቁ በርካታ ሰዎች መኖራቸው ታውቋል።
የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ " ሰኔ10/2022 ዓ.ም በታሕታይ ቆራሮ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የዓዲ-ገሽቲን ዓዲ-ሓበሳይን ጣብያዎች እንዲሁም ሰሜን ምዕራብና ምስራቅ ዞኖች ውስጥ ሞት ሲያጋጥም ሰዎችና እንስሳት መያዛቸው የሚያሳይ መረጃ አለኝ" ብሏል።
ይህን ተከትሎ ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO)፣ ከእርሻና ገጠር ልማት ቢሮ፣ እንዲሁም ከጤና ቢሮ የተውጣጣ ቡድን ሰኔ 22 2022 ሁኔታውን መርምሮ የመከላከል ስራ እንዲሰራ ተልኳል።
ቡድኑ ከእንስሳት ጋር ንክኪ ከነበራቸውና ስጋ ከበሉ 120 ሰዎች መካከል 34 በበሽታው እንደተያዙ እና ሁለት ደግሞ ህይወታቸው እንዳለፈ አረጋግጧል።
በበሽታው መያዛቸውከተጠረጠሩ 30 የቤት እንስሳት (ከብቶት፣ ፍየሎችና አህዮች) ውስጥ 23 ሞት እንዳጋጠመ ተገንዝቧል።
"በዳሰሳቸው 12 ወረዳዎችን ለማዳረስ የሞከሩ ሲሆን በመንገዳቸው ላይ 13 በአባ ሠንጋ የተያዙ ሰባት [አንድ ላዕላይ ማይጨው 12 ደግሞ ቆላ ተምቤን ውስጥ] አግኝተዋል" ይላል የክልሉ ጤና ቢሮ ለቢቢሲ የላከው መረጃ።
ክልሉ አክሎም በመገናኛ እጥረት ሳብያ ግን የህዝብ ጤና ስጋት አስተዳደር [Public health Emergency Management (PHEM)] ቡድን ከሁሉም ወረዳዎች የጤና ተቋማት ሙሉ መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል።
ከመጋቢት 2022 መጨረሻ ጀምሮ በማእከላዊ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ ምስራቅና ምስራቅ ዞኖች ውስጥ በጠቅላላ በአባ ሠንጋ መያዛቸው የተጠረጠሩ 116 ሰዎችና 7 ሞት እንደተመዘገበ የጤና ቢሮ ሪፖርት ያመለክታል።
2. የእብድ ውሻ በሽታ
ከጦርነቱ በፊት የእብድ ውሻ በሽታ ቁጥጥርና መከላከል ስራ በማህበረሰቡ፣ በመጀመርያ ደረጃ የጤና ክትትል ቡድን እንዲሁም ሆስፒታሎች ይሰራ ነበር።
በወቅቱ በርካታ የጤና ተቋማት በበሽታው ስለተጠረጠሩና ስላጋጠመ ሞት የሚያሳይ ሪፖርት ያቀርቡ ነበር።
የውሾች ክትባት፣ ባለቤት የሌላቸው ውሾች አስተዳደር፣ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች የሚደረግ ህክምና እንዲሁም የህዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በቀጣይነት ስኬታማ በሆነ መልኩ ይካሄዱ ነበር።
እስከ 2030 በእብድ ውሻ በሽታ የሚያጋጥም ሞት ዜሮ ለማድረስ እየተሰራ እንደነበር የትግራይ ክልል የጤና ቢሮ ያመለክታል።
"ይሁን እንጂ ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስና ከበባ በአሁኑ ወቅት በውሻ መነከስንና በበሽታው መያዝን የሚመለከት ሪፖርት ከ12 በመቶ በታች በሆኑ የጤና ተቋማት ብቻ ተገድቦ እንደሚገኝ" የትግራይ ክልል የላከው ሪፖርት ያሳያል።
"በአሁኑ ወቅት በውሻ መነከስና ያጋጠመ ሞትን የሚመለከቱ ይፋ የሆኑና ያልሆኑ ሪፖርቶች ወደ ቢሮው እየመጡ ነው” የሚለው የትግራይ የጤና ቢሮ፣ በጦርነቱ ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለውሾች የሚሆን ክትባት፣ ባለቤት የሌላቸው ውሾችን ለማስወገድ የሚውል ‘ስትሪክኒን’ የሚባል ኬሚካል እንዲሁም የተያዙ ሰዎችን ለማከም የሚረዳ የመድሃኒት አቅርቦት እንደሌለ አስረድቷል።
በዚህም ምክንያት በ11 የትግራይ ወረዳዎች 41 ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። እንዲሁም በበሽታው የታመሙ ሰዎች ለማከም የሚረዳ መድሃኒት ባለመኖሩ በበሽታው የተያዙ ሰዎች በቤታቸው በባህላዊ መንገድ አልያም ወደ ባህላዊ ሐኪም በመሄድ መፍትሔ ለማግኘት እንዲጥሩ እያስገደዳቸው ነው።
3. ወባ
በትግራይ ክልል የወባ ወረርሽኝ ከመስከረም -እስከ ታሕሳስ ባለው ወቅት እጅግ ስፋት ባለው ሁኔታ የሚታይ ሲሆን፤ በሚያዝያ እና ግንቦት ወራትም ያጋጥማል።
በክልሉ ለመጨረሻ ጊዜ ወረርሽኝ የተከሰተው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ ሲሆን አካባቢውም አሕፈሮም የሚባል ወረዳ ነበረ።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የወባ በሽታ የመከላከል እና የቁጥጥር ስትራቴጂዎች በተገቢው መንገድ በመተግበራቸው የበሽታው ወረርሽኝ አጋጥሞ አያውቅም።
አሁን ላይ በጦርነቱ ሳቢያ ተገቢ የህክምና አገልግሎት፣ የህክምና አቅርቦቶች እና መደበኛ ክትትል ባለመኖሩ የበሽታው መስፋፋትና በበሽታው ምክንያት የሚያጋጥም ሞት እየተመዘገበ መሆኑ የክልሉ ቢሮ ለቢቢሲ ገልጿል።
ወረርሽኙን ለመከላከል እና ህይወትን ለማዳን ቀድሞ ስለበሽታው መስፋፋት ማወቅ እና የታካሚ መረጃ ማግኘት ወሳኝ መሆኑን የጤና ቢሮው ይገልጻል።
ነገር ግን በትግራይ የመገናኛ ዘዴዎች አገልግሎት በመቋረጡ እና ከየአካባቢው የሚቀርቡ መረጃዎች ያልተሟሉ በመሆናቸው የበሽታው መስፋፋት በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት እንዳዳገተው ገልጿል።
ወባ ከሰኔ 2020 ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ በወረርሽኝ መልክ እየተዛመተ መሆኑን የትግራይ ጤና ቢሮ ያስረዳል።
የበሽታውን ሁኔታ የሚያጠና የባለሙያዎች ቡድን ወደ ተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እንደተላኩ የሚገልፀው ጤና ቢሮው "ለቡድኑ ጉዞ የቀረበ የነዳጅ እና የገንዘብ ድጋፍ መቀለ በሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት ፅህፈት ቤት የተሸፈነ ነው። ሆኖም ግን በነዳጅ እና በጊዜ እጥረት የበሽታውን ዋና መንስኤ መለየት አልቻሉም” ብሏል።
እ.ኤ.አ. እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2022 ባለው ጊዜ በትግራይ ውስጥ ከ10 በላይ ወረዳዎች የወባ በሽታ መስፋፋት ታይቷል። በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የፀረ ወባ መድሐኒት እና ሌሎች የህክምና አቅርቦቶች ባለመኖሩም ሁኔታው ተባብሷል።
ወረርሽኙን በጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ ወደ ብዙ የትግራይ አካባቢዎች ሊዛመት እንደሚችል ነው የትግራይ ጤና ቢሮ ያስጠነቀቀው።












