ድርቅ ባጋለጠው ወንዝ ውስጥ 450 ኪ.ግ. የሚመዝን ቦምብ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጣሊያን በድርቅ ምክንያት በደረቀ ወንዝ ውስጥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተጠምዶ ያልፈነዳ ግዙፍ ቦምብ ተገኘ።
450 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ቦምቡ ወንዙ ውስጥ የታየው በድርቅ ምክንያት የወንዙ የውሃ መጠን ከቀነሰ በኋላ ነው። ጣሊያን ከ70 ዓመታት ወዲህ አስከፊ ነው ያተባለው ድርቅ ካጋጠማት በኋላ አሳ አስጋሪዎች ፖ ከተሰኘው ወንዝ ቦምብ አግኘተዋል።
ይህ 650 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ወንዝ አብዛኛው ክፍሉ ደርቋል። “አሳ አስጋሪዎች ቦምቡን ከፖ ወንዝ ዳርቻ አግኝተዋል” ሲሉ የጣሊያን ጦር ኮሎኔል ማርኮ ናሲ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። የጣሊያን ጦር ባለስልጣናት 450 ኪሎ ግራም ከሚዘዝነው ቦምብ 240 ኪሎ ግራሙ ተቀጣጣይ እንደሆነም ይፋ አድርገዋል።
ባለሙያዎቹ ቦምቡን ከወንዙ ውስጥ ከማስወጣታቸው በፊት በአካባቢ ይኖሩ የነበሩ ከ3ሺህ በላይ ሰዎችን ቀድመው ማስወጣት ነበረባቸው። የጣሊያን መንግሥት ነዋሪዎችን ከማስወጣት በተጨማሪ በአካባቢው የአየር ክልል ለተወሰነ ጊዜ ዘግቶም ነበር። ፖ በጣሊያን ረዥሙ ወንዝ ሲሆን በጣሊያን የግብርና ስራ ውስጥ ሲሶ የመስኖ ሥራ የሚከናወነው ከዚህ ወንዝ በሚገኝ ውሃ ነው።
የሳተላይት ምስሎች በጣሊያን ባጋጠመው ድርቅ ምክንያት የደረቁ የወንዙን ክፍሎችን አሳይተዋል።
ጣሊያን ያጋጠማትን አስከፊ ድርቅ ተከትሎ ከአንድ ወር በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃ ነበር።








