የእስራኤል ጦር ክፍሎች የሰብአዊ መብቶችን እንደጣሱ አሜሪካ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
አምስት የእስራኤል ጦር ክፍሎች በግለሰቦች ላይ ባነጣጠሩ የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንደፈጸሙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሆኖም እነዚህ የጦር ክፍሎች አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ማግኘታቸውን ይቀጥላል ተብሏል።
ሁሉም ክስተቶች ከጋዛ ውጭ መሆኑን እና ከአሁኑ ጦርነት በፊት መሆናቸው ተነግሯል።
እስራኤል በአራት የጦሩ ክፍሎች የእርምት እርምጃ መውሰዷን እና በአምስተኛው ላይ "ተጨማሪ መረጃ" መስጠቷንም አስታውቋል።
በዚህ ምክንያትም ሁሉም የጦር ክፍሎች ለአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ ብቁ በመሆናቸው ይቀጥላሉ ተብሏል።
አሜሪካ በዓመት 3.8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሣሪያዎችን እና የመከላከያ ሥርዓቶችን ለእስራኤል በማቅረብ ዋና ወታደራዊ አጋሯ ናት።
አሜሪካ በየትኛውም የእስራኤል የጦር ክፍል ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ ስትሰነዝር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቬዳንት ፓቴል አምስት የጦሩ ክፍሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ብለዋል።
"ከእነዚህ ክፍሎች ውስጥ አራቱ ጥሰቶቹን አስተካክለዋል። ይህም አጋሮች እንዲያደርጉት የምንጠብቀው ነገር ነው" ብለዋል።
"ስለቀሪው የጦር ቡድን ከእስራኤል መንግስት ጋር እየተመካከርን እና እየተገናኘን እንቀጥላለን። ክፍሉን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ አቅርበዋል።"
"ከእነሱ ጋር በአንድ ላይ እየተሳተፍን ነው። ሂደቱ ሲጠናቀቅ በጦር ቡድኑ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ እንወስዳለን" ብለዋል ፓቴል።
ሁሉም ክስተቶች በቅርብ ዓመታት ውስጥ በዌስት ባንክ እና በእየሩሳሌም መፈጸማቸው ይታመናል።
እአአ በ1997 በሴናተር ፓትሪክ ሌሂይ የተነደፈው “የሌሂይ ህግ” የውጭ ወታደራዊ ክፍሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ ከአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ ማግኘት ሊቋረጥ እንደሚችል ይገልጻል።
የአሜሪካ መንግስት ማሰቃየትን፣ ከፍርድ ውጪ ግድያን፣ በግዳጅ መሰወርን እና አስገድዶ መድፈርን እንደ ጥሰት በመቁጠር የልሂይ ህግን ተግባራዊ ያደርጋል።
እንዲህ ዓይነት ግኝት በሚኖርበት ጊዜም ቢሆን ግን ጉዳዩ በትክክል ታይቶ ፍትህ እንዲሰፍን ከተደረገ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጉዳዩን ወታደራዊ እርዳታውን የሚቀጥልበት ዕድል አለ።
እስራኤል ከአምስቱ ክፍሎች በአራቱ ላይ ይህንን አድርጋለች ብሏል። ሚኒስቴሩ ስለ ጥሰቶቹ፣ ስለማስተካከያ እርምጃው፣ ስለተሳተፉት ክፍሎች ወይም ማሻሻያው ውጤታማ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
አሜሪካ ለአምስተኛው የጦር ክፍል የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታቋርጥ ለማስታወቅ አፋፍ ላይ ነበረች ቢባልም ከእስራኤል አዲስ መረጃ በመገኘቱ ውሳኔው ዘግይቶ እንዲሰጥ ይደረጋል ተብሏል።
ጥሰቱን የፈጸመው እአአ በ1999 የተመሰረተው እና አክራሪ አይሁዶች ብቻ የሚያገለግሉበት ልዩ የወንዶች የጦር ክፍል ሆኖ የተቋቋመው የኔትዛህ ይሁዳ የጦር ጭፍራ እንደሆነ በሰፊው ተዘግቧል።
እአአ በ 2022 በዌስት ባንክ በተደረገ ፍተሻ ወቅት በወታደሮች ታስረው በነበሩት የ80 ዓመቱ ፍልስጤማዊ-አሜሪካዊ ኦማር አሳድ ሞት ምክንያት እስራኤል ጭፍራው ላይ ምርመራ አከናውናለች።
በወቅቱ ዩናይትድ ስቴትስ "የተሟላ ምርመራ እና ሙሉ ተጠያቂነት" እንዲኖር ጠይቃ ነበር።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በአሳድ ሞት መጸጸቱን ገልጾ፤ አንድ አዛዥ “ተግሳጽ እንደደረሰው” እና ሁለት ወታደሮች ደግሞ ለሁለት ዓመታት ከከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ይታገዳሉ ቢልም በሦስቱም ላይ ክስ እንደማይመሰረትባቸው ታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሊሂይ ህግ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊፈረጅ ስለሚችል የእስራኤል ጦር ክፍል ስለመኖሩ ከቀናት በፊት ተጠይቀው “ውሳኔ ወስኛለሁ። በሚቀጥሉት ቀናት ሊታወቅ ይችላል” ብለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በአገሪቱ ጦር ላይ የሚጣለውን ማንኛውንም ማዕቀብ ውድቅ እንደሚያደርጉት ገልፀው “በሙሉ ኃይላችን እንታገላለን” ብለዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት እና የጦር ካቢኔ ሚንስትሩ ቤኒ ጋንትዝ ከብሊንከን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ለአምስተኛው ወታደራዊ ክፍል እርዳታውን ለማቋረጥ የነበረውን አቋም አዘግይቷል ወይም አለሳልሷል በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከእስራኤል መንግሥት ጋር የሚያደርጉት ምክክር ሲጠናቀቅ ባለሥልጣናት ውሳኔ ያስተላልፋሉ ሲሉ ፓቴል ምላሽ ሰጥተዋል።












