ከሩሲያ የተባረሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጀርመን ዜጎች አገሪቱን ሊለቁ ነው

ሩሲያ እና ጀርመን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በትምህርት እና የባሕል ዘርፎች ላይ ይሠሩ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጀርመን ዜጎች በቀጣይ ሳምንታት ሩሲያ ለቀው እንደሚወጡ ተገለጸ።

ቀድም ሲል አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የፑቲን አስተዳደር በሩሲያ ተቀጥረው የሚሠሩ የጀርመን ዜጎች ቁጥርን ለመገደብ ስለመወሰኑ ዘግበው ነበር።

በቀጣይ ሳምንታት ከሩሲያ የሚባረሩት የጀርመን ዜጎች በሞስኮ የሚገኝ የጀርመን ትምህርት ቤት መምህራን እና የባሕልና የኪነ ጥበብ ማዕከል የሆነው ጎተ ኢንስቲትዩት ሠራተኞች መሆናቸው ተመልክቷል።

ሞስኮ የጀርመን ዜጎችን ከአገሯ የምታባርረው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በዩክሬን ጦርነት ምክንያት መሻከሩን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ወር ሁለቱም አገራት በእያንዳንዳቸው ኤምባሲዎች ሠራተኞች የነበሩ 40 ሰዎች 'ተቀባይነት የሌላቸው' ሲሉ ከአገር አሰናብተዋል።

አንድ የጀርመን ጋዜጣ በአሁኑ ዙር ከሩሲያ የሚባረሩ ሰዎች ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠር መሆኑን እና ከእነዚህም መካከል ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የሌላቸው በሌላ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች እና ዲፕሎማቶች እንደሚገኙበት ዘግቧል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ በርካታ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከአገራቸው አባረዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት በስለላ ወንጀል የተጠረጠሩ ከ40 የማያንሱ ዲፕሎማቶች ከአራት የአውሮፓ አገራት እንዲወጡ ተደርገው ነበር።

ጠንካራ የኢኮኖሚ እና ባሕል ትስስር የነበራቸው ጀርመን እና ሩሲያ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ግንኙነታቸው ሻክሮ ይገኛል።

ሞስኮ በኪዬቭ ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ የጀርመኑ ቻንስለር ለጀርመን ጦር በጀት ከመጨመር አልፈው ለዩክሬን በቀጥታ የጦር መሣሪያዎችን መላክ ተያይዘዋል።

መራሄ መንግሥት ኦልፍ ሽሎዝ አገራቸው 'ሊኦፓርድ 2' የተሰኙ ታንኮችን ለዩክሬን እንደምትልክ ይፋ ሲያደርጉ ሩሲያ ጀርመንን አጥብቃ ከተቸች በኋላ ሞስኮ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚ የፈጸመውን የጦር ወንጀል በማስታወስ በርሊን ታሪካዊ ኃላፊነቷን መወጣት ዘንግታለች ብላለች።

ሾልዝ ግን አገራቸው ጀርመን አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ዩክሬንን መርዳቷን እንደምትቀጥል በመግለጽ 2.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።