የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማፂያንን ለመዋጋት ኬንያ ጦር ልታሰማራ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኬንያ የመጀመሪያ የሆነውን የቀጠናውን የሰላም አስከባሪ ጦር አባላት ወደ ምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ልታሰማራ መሆኑ ተገለጸ።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቀጠናው ጦር ጋር የሚቀላቀሉትን የኬንያ መከላከያ ሰራዊት አባለትን ስንብት ስነ ስርዓትም በዛሬው እለት ያካሂዳሉ ተብሏል።
በዛሬው ዕለት በሚካሄደው የሰንደቅ አላማ የመስቀል ስነስርዓት ይኖራል።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚሰማራው የኬንያ ጦር የምስራቅ አፍሪካ ማብረሰብ አካል በመሆን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦር በአገሪቱ ግጭትና ሁከትን ለማስቆም የሚያደርገውን ጥረት ያግዛል ተብሏል።
አንዳንድ የኬንያ ወታደሮች ቀድመው ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያቀኑ ሲሆን በአማፂያኑ ላይ ለታቀደው ዘመቻም የሎጂስቲክስ ድጋፎችን ከመስከረም ጀምሮ እያደረጉ ይገኛሉ።
የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አባል ሃገራት በያዝነው አውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ላይ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያሉ አማጽያንን ለመዋጋት ወታደሮችን የማሰማራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የኬንያ ጦር ሰራዊት የመጀመሪያ ተልዕኮ በሰኔ ወር በኤም 23 አማፂያን ቁጥጥር ስር ያለችውን የድንበር ከተማ ቡናጋናን መልሶ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ዘመቻ ማገዝ ይሆናል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሩዋንዳ የኤም 23 አማፂያንን ቡድንን ትደግፋለች በማለት የምትወቅስ ሲሆን ሩዋንዳ በበኩሏ እነዚህ ከሶች ሃሰት ናቸው ስትል በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።












