ከባድ የተባለው አውሎ ነፋስ በአሜሪካ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

ታትሟል

ኢያን የተባለው ከባድ አውሎ ነፋስ የአሜሪካዋን የፍሎሪዳ ግዛት መትቶ ከፍተኛ ውድመት ካደረሰ  በኋላ ደቡባዊ ላሮላይናን መትቷል።

ከባሕር ላይ የተነሳው ኢያን አውሎ ነፋሱ በጆርጂጅ ትላንት አርብ መልሶ ከተከሰተ በኋላ ከባድ ውድመት የማድረስ አቅሙ ቀንሶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች አቅንቷል።

ነገር ግን የሚያስከትለው አደጋ ገና አላበቃም። በዚህም ፍሎሪዳን ጨምሮ በአካባቢዋ ለቀናት የሚቆይ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ተተንብይዋል።

ትላንት አርብ ጠዋት በፍሎሪዳ 21 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የፍሎሪዳ የአደጋ ጊዜ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ሆኖም ግን የብሔራዊው የጤና ምርመራ ባለሙያዎች ሁሉም ሞቶች ከአውሎ ንፋሱ ጋር በቀጥታ የተገናኙ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

በሚያስከትለው ጉዳት በደረጃ አራት ላይ የሚቀመጠው ኢያን የተባለው አውሎ ነፋስ ረቡዕ ዕለት ፍሎሪዳን ሲመታ አስካሁን አሜሪካንን ካጋጠማት ተመሳሳይ አደጋ አንጻር ጠንካራ የሚባለው ነው።

አውሎ ነፋሱ በደቡባዊ ካሮላይና የባሕር ዳርቻዎች ላይ የተገነቡ አራት የማዕበል መከላከያዎችን አፍርሶ ታዋቂውን የባሕር ዳርቻ ከተማዋን ሚርትልን ጨምሮ አከባቢውን በጎርፍ አጠለቅልቋል።

ክስተቱ እስከ አርብ ምሽት ድረስ በበደቡባዊ ካሮላይና 200 ሺህ የሚጠጉ መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት የኤሌትሪክ አቅርቦት እንዲቋረጥባቸው ምክንያት ሆኗል።

የሚምዘገዘግ አውሎ ከተከሰተበት አካባቢ 130 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ቻርልስተን በተባለች ከተማ ተሽከርካሪዎች በጎርፍ በተዋጠ መንገድ ላይ ሲጓዙ ታይተዋል።

አውሎ ነፋሱ ወደ ሰሜን አቅጫ በሰዓት 85 ኪሎ ሜትር ሲከንፍ እንደነበር የአሜሪካ ብሔራዊ የሄሪከን መከታተያ ማዕከል አሳውቋል።

‘ኢያን’ አርብ ላይ ጥንካሬው ቀንሶ እንደታየ የገለጸው ማዕከሉ አደገኝነቱ ግን አልቀነሰም ብሏል።

ማዕከላዊ ፍሎሪዳ ላይ በሚቀጥለው ሳምንት በማይታወቅ ደረጃ ወንዞች ሊሞሉ እና ከባድ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችልም አመልክቷል።

በተጨማሪም ማዕከሉ ‘ኢያን’ አውሎ ነፋስ ወደ ሰሜን አቅጫ ተጉዞ ወደ ሰሜን ካሮላይና እና ቨርጂኒያ ሊደርስ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ገልጿል።

አውሎ ነፋሱ ወደ ሰሜን ካሮላይና ወይም ቨርጂኒያ አቅጣጫ በመዞር ቅዳሜ ማምሻው ላይ እንደሚጣፋ ይጠበቃል።

በአጠቃላይ በፍሎሪዳ አውሎ ነፋሱ ያስከተለው ጉዳት 1.6 ሚሊዮን ሕዝብን የኤልክትሪክ አቅርቦቱ እንዲቋረጥበት አድርጓል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትላንት በዋይት ሐውስ ባደረጉት ንግግር “የአደጋውን መጠን መመልከት እየጀመርን ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ‘ኢያን’ በአሜሪካ ታሪክ ከታዩት እጅግ አስከፊ የተፈጥሮ አደጋዎች አንዱ ሊሆን ይችላልም ብለዋል።

አንድ ጥናት አውሎ ነፋሱ 47 ቢሊዮን ዶላር የኢንሹራንስ ኪሳራ ማድረሱን አመላክቷል።

‘ሄሪኬን ኢያን’ አውሎ ነፋስ በምድብ አምስት ከሚቀመጠው እና ‘ሄሪኬን ካትሪና’ ከተባለው አውሎ ነፋስ ያነሰ ጉዳት አድሷል።

ካትሪና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2005 የልዊዛኒያ ግዛትን በመታበት ጊዜ 1 ሺህ 800 ሰዎች የገደለ ሲሆን 125 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመትን አድርሷል።

በፍሎሪዳ በዚህ ሳምንት በደረሰው ጉዳት መጀመሪያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የተቋረጠው በፎርት ሜርስ ባሕር ዳርቻ ሲሆን፣ ከሁለት ቀናት በኋላ በባሕር ዳርቻው አቅራቢያ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ለተመለሱት ፓት እና ካቲሊን አንገር ላሉ ሰዎች ድንጋጤን የፈጠረ ነው።

“ሊፍት፣ መዋኛ ገንዳው ጋር የነበረው ቤት፣ ቢሮ፣ እና ቤተ መጽሐፍቱ የለም። ተወስዷል” የሚሉት አንገር “የመኪና ማቆሚያው የለም። ከህንጻዎቹ በስተቀር ሁሉም ሄዷል። የቀረ ነገር የለም” ሲሉ አክለዋል።

በፎርት ሜርስ በሚገኘው እና ካሉሳጃቺ በታባለው ወንዝ ዳር ባለ አነተኛ ወደብ 30 የሚጠጉ ጀልባዎች ወደመዋል።

ብስጭቱ ፊቱ ላይ የሚበብ አንድ ግለሰብ “በጅልባ ነበር የምተዳደረው። በእርግጥ በጀልባ ሥራ ነበር የምተዳደረው ልበል። ነበር። ”

በሌላ በኩል በኩባ ‘ኢያን’ ባስከተለው ጉዳት በመላው አገሪቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በመቋረጡ 11 ሚሊዮን ሕዝብ የኃይል አገልግሎት እያገኘ አይደልም።

ሦስት ቀን ያስቆጠረውን የኤሌክትሪክ መቋረጥ በመቃወም ነዋሪዎች በአገሪቱ ዋና ከተማ ሃቫና ወደ ጎዳናዎች ወጥተዋል።