ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ አስጊ መሆኑን የአውሮፓ ህብረት አስጠነቀቀ
ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት እንደገና ማገርሸቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ በአስከፊ ደረጃ መባባሱን የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ።
የአውሮፓ ህብረት የክራይሲስ ማኔጅመንት ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርሲክ ጦርነቱ ከማገርሸቱ በፊት የሰብዓዊ ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደነበር ገልጸው አሁን የበለጠ መክፋቱን ገልጸዋል።
“ጦርነቱን ማገርሸቱን ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ በከፋ ደረጃ መባባሱ የአውሮፖ ህብረትን ያሳስበዋል” ብለዋል ኮሚሽነሩ።
እንደ አዲስ ባገረሸው ጦርነት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ አዲስ የተፈናቀሉ ሲሆን በነዋሪዎች ንብረት እና መሰረተ ልማት ላይ መጠነ ሰፊ ውድመት እየደረሰም ነው ተብሏል።
ህብረቱ በክልሉ የሰብዓዊ ሁኔታው ቀድሞውንም አስከፊ ሁኔታ ላይ የነበረውንም ወደበለጠ ቀውስ ይከተዋል ብሏል።
የጦርነቱ ማገርሸት በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በእጅጉ እንቅፋት ሆኗል ብሏል ህብረቱ። መሰረታዊ ሸቀጦች፣ የነዳጅ እና የገንዘብ አቅርቦት በትግራይ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የቀጠለ ሲሆን ጦርነቱ በተዛመተባቸው የአማራ እና አፋር አካባቢዎች እንዲሁ ይህ ችግር እየታየ ነው ብሏል።
በነዚህ አካባቢዎች የረድዔት ሰራተኞች ስራቸውን ለማቆም የተገደዱ ሲሆን ሰራተኞቻቸውን ከነዚህ አካባቢዎች አስወጥተዋል።
ይህ ሁኔታ በትግራይ፣ በአፋር እና አማራ ክልሎች በጦርነቱ የተጎዱ በሰብዓዊ እርዳታ ጥገኛ ለሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከባድ ጉዳት መሆኑንም አፅንኦት ሰጥቷል።
በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች 13 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እርዳታ ፈላጊ እንደሆነ የአለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአራት አስርት አመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፋ ድርቅ የተመታች ሲሆን በዚህም 7.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት ተዳርገዋል።
የአለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግን በተከተለ መልኩ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች እርዳታ ለሚያቀርቡ የረድዔት ድርጅቶች ያለምንም እንቅፋት እርዳታ እንዲያስገቡ የአቅርቦት መንገድ እንዲከፍቱ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ህብረቱ ተፋላሚ ወገኖች የሰላማዊ ዜጎች፣ የረድዔት ሰራተኞችን እና አቅርቦቶችን ደህንነት የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለባቸው ህብረቱ አስታውሶ ተፋላሚ ወገኖች ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቋል።
ጦርነቱ ከተነሳበት ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙ የአለም አቀፍ ሰብዓዊ የህግ ጥሰቶችን አውግዞ ሁሉም ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙና በድርድር ላይ የተመሰረተ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርቧል።