እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ገድላ አራት ዜጎቿን ከእገታ ነጻ አወጣች

ታትሟል

የእስራኤል ጦር “እጅግ ውስብስ” በተባለ ወታደራዊ ዘመቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ገድሎ አራት ዜጎቹን ከሐማስ እገታ ነጻ ማውጣቱ ተገለጸ።

የ22፣ 26፣ 27 እና 41 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አራት እስራኤላውያን በሐማስ የታገቱት ቡድኑ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ነበር።

የእስራኤል ወታደሮች ቡሴሪያት በተባለ አካባቢ በአየር ኃይላቸው ታግዘው ከሐማስ ጋር ከፍተኛ ውጊያ አድርገዋል።

የእስራኤል ጦር “አደገኛ እና ውስብስብ ዘመቻ” ብሎ በገለጸው ወታደራዊ ዘመቻ ከ100 ያልበለጡ ፍልስጤማውያን ሳይሞቱ አልቀረም ብሏል።

የፍልስጤም ባለስልጣናት ግን በአየር ድብደባው እና አል-ኑሴኢራት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አካባቢ በተደረገ ውጊያ ቢያንስ 210 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ400 በላይ መቁሰላቸውን እየገለጹ ነው።

እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻውን ካካሄደች በኋላ ከአካባቢው የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከፍተኛ ውድመት የደረሰበትን አካባቢ አሳይተዋል። ሆስፒታሎች በተጎጂ ሕጻናት እና ሴቶች ተጨናንቀው፤ ሐኪሞች ለሁሉም ተጎጂ ሕክምና ማቅረብ ሲሳናቸው አሳይተዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ ይህ “በደኅንነት መረጃ ላይ የተመሰረተ ዘመቻ” የተከናወነው በአገሪቱ ጦር፣ በእስራኤል የደኅንነት ኤጀንሲ እና በእስራኤል ፖሊስ ጥምረት መሆኑን ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ታጋቾቹ ነጻ የወጡት በአካባቢው ከነበሩ ሁለት ሕንጻዎች መሆኑን ተናግረው፤ በዘመቻው ወቅት ከፍተኛ ተኩስ እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

በዚህም በቦታው ላይ አንድ የእስራኤል የልዩ ኃይል አባል ቆስሎ ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ አልፏል ብለዋል።

የእስራኤል ጦር ከ8 ወራት በኋላ ከእገታ ነጻ የወጡት አራቱም ታጋቾች በመልካም የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን አስታውቋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በዘመቻው የተሳተፉ አካላትን አሞካሽተው፤ “በሕይወት ያሉትንም ይሁን በሕይወት የሌሉትን ታጋቾች ወደ አገራቸው ሳንመልስ ዘመቻችንን አይጠናቀቅም” ብለዋል።

የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ደግሞ ለ47 ዓመታት የእስራኤል ጦር ውስጥ ሳገለግል እንደዚህ አይነት “በጀግንነት የላቅ ዘመቻ ሲከናወን ስመለከት የመጀመሪያዬ ነው” ብለዋል።

ሲቢኤስ በበኩሉ በዚህ ዘመቻ ላይ የአሜሪካ የደኅንነት ተቋም ለእስራኤል ባለስልጣናት መረጃ ስለማቀበሉ ሁለት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሐማስ መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ከ1ሺህ 200 በላይ ሰዎችን ገድሎ ወደ 251 ሰዎችን አግቶ መውሰዱ ይታወሳል።

ከእነዚህ መካከል 116 ሰዎች አሁንም በፍልስጤም የሚገኙ ሲሆን የአገሪቱ ጦር ቢያንስ 41 የሚሆኑት ሕይወታቸው ሳያልፍ አይቀርም ይላል።

ሕዳር መጀመሪያ ላይ በተደረሰ ስምምነት 105 ታጋቾች በሐማስ ተለቀዋል።

እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ባለችው ጥቃት አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ 36 ሺህ 801 ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።