ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የሚካሄደው ንግግር እስከ አርብ እንደሚቀጥል ተነገረ
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በናይሮቢ የቀጠለው ንግግር እስከ አርብ ሊቆይ እንደሚችል ተነገረ።
የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ሰኞ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም. በሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች አማካይነት መካሄድ የጀመረው ንግግር ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 30/2015 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።
በኬንያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና በህወሓት ተወካዮች መካከል እየተካሄደ ያለው ንግግር አስከ አርብ ኅዳር 03/2015 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል።
በተጨማሪም በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ ምንጮች ንግግሩ ዛሬ ረቡዕ እንደማይጠናቀቅ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እየተካሄደ ያለው ንግግር በተያዘለት ጊዜ ረቡዕ ሊያበቃ የሚችልበት ዕድል ጠባብ በመሆኑ ሁለት ቀናትን ጨምሮ አስከ አርብ ሊቀጥል እንደሚችል ቢቢሲ ከዲፕሎማቱ ለመረዳት ችሏል።
ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ በሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች መካከል እየተካሄደ ያለው ንግግር በዝግ እየተደረገ ሲሆን አስካሁን ስላለው ሂደትና ስለደረሱበት ውጤት የተባለ ነገር የለም።
ውይይቱ ወደሚካሄድበት የናይሮቢ፣ ካረን ሞራን ማዕከል ከሁለቱ ወገኖች እና ከአሸማጋዮች በስተቀር መግባት የማይቻል ሲሆን፣ በንግግሩ ማጠቃለያ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነትን ለማንቃት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ከአንድ ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ድርድር በተመሳሳይ ከተያዘለት ጊዜ ተጨማሪ ቀናትን መውሰዱ ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ጦርነት ለማብቃት ቋሚ ግጭት የማስወገድ እና ትጥቅ የመፍታት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ረቡዕ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ የእርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመርና የአገሪቱ ድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕግ እንዲከበር የማድረግ አላማ አለው።
ለአስር ቀናት የቆየውና በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ተወካዮች መካከል ሲካሄድ የቆየው ንግግር ማብቂያ ላይ፣ ሁለቱም ወገኖች የደረሱበትን 12 ነጥቦችን የያዘ ባለ ሁለት ገጽ ስምምነት በጋራ ይፋ አድርገዋል።
ከዚህም በኋላ ሁለቱም ወገኖች ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ተከታታይ ንግግሮችን ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸው ነበር።
በዚህም መሠረት ትጥቅ መፍታትን፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን፣ መሠረታዊ አገለግሎትን ማስጀመርና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ለመነጋገር የሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ የጦር አዛዦች ናይሮቢ ላይ እየተናጋገሩ ይገኛሉ።
የፌደራል መንግሥቱን የመከላከያ ኃይል በመወከል ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ በተገኙበት ሰኞ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም. በናይሮቢ ንግግሩ ተጀምሯል።