የቼቺኒያው መሪ ታዳጊ ልጆቹን ከሩሲያ ጎን ለማሰለፍ ወደ ጦር ሜዳ እንደሚልክ ገለጸ

ታትሟል

የቼቺኒያው መሪ ራምዛን ካዲሮቭ የ14፣ የ15 እና የ16 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ልጆቹ ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ በምታካሂደው ጦርነት እንዲዋጉ ወደ ጦር ሜዳ እንደሚልክ ገለጸ።

የቭላድሚር ፑቲን ጠንካራ አጋር የሆነው ራምዛን ካዲሮቭ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ፤ አንድ አባት ልጆቹ ቤተሰባቸውን፣ ሕዝብን እና አባት አገራቸውን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ማስተማር አለበት ብሏል።

ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን በጦርነት ላለማሳተፍ ሩሲያ የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት ፈራሚ ነች።

ከዚህ በተጨማሪም የዓለም ወንጀለኞች ፍርድ ቤትም ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን በቀጥታ በጦርነት ማሳተፍን እንደ የጦር ወንጀል ይቆጥረዋል።

የቼቺኒያው መሪ ግን ረዘም ባለ ጽሑፉ ልጆቹ ገና በለጋ ዕድሜያቸው የጦር ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጾ፣ በጦር ግንባር የሚፈተኑበት ጊዜ ታቀርቧል ብሏል።

ራምዛን ካዲሮቭ በቴሌግራም ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፉ ላይ ልጆቹ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ሲተኩሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አብሮ አያይዟል።

ካዲሮቭ እአአ 2007 በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከተሾመ ወዲህ የደቡብ ሩሲያ ክፍልን ሲያስተዳድር ቆይቷል።  

የቼቸን ኃይሎች የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለሞስኮ ወግነው ሲዋጉ የቆዩ ሲሆን፣ ካዲሮቭ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የኒውክሌየር ጦር መሳሪያን ጨምሮ ጠንከር ያለ እርምጃ እንድትወስድ ሲወተውት ነበር።

የቼቺኒያው መሪ ይህን አስተያየት የሰጠው የሩሲያ ጦር ይዞት ከነበረው ቁልፍ የዩክሬን ከተማ ማፈግፈጉ ከተገለጸ በኋላ ነው።

የዩክሬን ጦር በዶኔስክ ግዛት የምትገኘውን ለይማን ከተማን መያዛቸው ሌሎች በሩሲያ ጦር ተይዘው የሚገኙ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ ቁልፍ እንደሆነ ይገለጻል።

ይህች ከተማ የሩሲያ ጦር የሎጂስቲክ ማዕከል ሆና ስታገለግል ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንት ሩሲያ ሕዝበ ውሳኔ አካሂጃለሁ በማለት ዶኔስክ፣ ሉሃንስክ፣ ዛፖሪዢያ እና ኼርሶን የተባሉትን የዩክሬን ግዛቶችን ጠቅልላ የራሷ አካል ማድረጓን አስታውቃ ነበር።

ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ግን ይህን ሕዝበ ውሳኔ ሐሰተኛ ሲል አጥብቀው አጣጥለውታል።