ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩኬዋ ግዛት የዩክሬን ስደተኞችን ለሚቀበሉ ቤተሰቦች በየወሩ 93 ሺህ ብር መስጠት ጀመረች
የዩናይትድ ኪንግደም ግዛት የዩክሬን ስደተኞችን በቤታቸው ተቀብለው ለሚያስጠልሉ በጎ ፈቃደኛ ቤተሰቦች 600 ፓውንድ ወይም 93 ሺህ ብር በየወሩ መውሰድ ይችላሉ አለች።
ይህ ክፍያ ቤተሰቦቹ እያደረጉት ላለው በጎ ተግባር “ለማመስገን” እንደሆነ ግዛቲቷ ገልጻለች።
ኤልምብሪጅ ቦሮው የተሰኘችው ግዛት አስተዳደር ቤታቸውን ከፍተው ዩክሬናውያንን እየተቀበሉ ላሉ ቤተሰቦች ገንዘብ መስጠት የጀመረው ከምስጋናው በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱንም ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን አክሏል።
በኤልምብሪጅ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ከ300 በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች ወደ 600 የሚጠጉ ዩክሬናውያንን ተቀብለው ድጋፍ አድርገዋል።
“ነዋሪዎች ድጋፍ የሚያደርጉት ገንዘብ ለማግኘት አይደለም” ሲሉም ስደተኞችን የሚቀበለው ኤልምብሪጅ ካን የተሰኘ አነስተኛ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተባባሪ ዳይሬክተር ጄኒ ትዊዲ ተናግረዋል።
“ነገር ግን ነዋሪዎች ሌላ ተጨማሪ ሰዎችን በቤታቸው ሲቀበሉ ወጪዎች መጨመራቸው ስለማይቀር ምክር ቤቱ ገንዘብ መስጠቱ በጣም ጥሩ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ስደተኞችን የተቀበሉ እና ሊቀበሉ ለሚያስቡ ነዋሪዎች “ሁሉም ሸክም በእነሱ ጫንቃ ላይ እንዳልሆነ” እና “በአካባቢው እነሱን የሚደግፍ ማህበረሰብ እንዳለ” እንዲያውቁ ለአካባቢው የዜና ወኪል ገልጸዋል።
ለሶሪያ ስደተኞች ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በአውሮፓውያኑ 2016 የተቋቋመው ኤልምብሪጅ ካን የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር ስደተኞች ወደ ማህበረሰቡ እንዲዋሃዱ ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅት ነው።
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ስደተኞችን የሚቀበል ማዕከል ያለው ሲሆን በተጨማሪም የማስተርጎም ተግባራትን እና ስደተኞችን ለሚቀበሉ የድጋፍ ሰጪ ኔት ወርክ አለው።
“ስደተኞች ስራ እንዲያገኙ ለመርዳት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማሪያ የማህበረሰብ እገዛ እንዲሁም በዚህ ያለውን ኑሮ እንዲረዱ የሚሰሩ ወደ 100 የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞች አሉን” ሲሉ ትዊዲ ገልጸዋል።