ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የናይጄሪያ ጦር በታጣቂዎች የታገቱ 33 ሰዎችን ማስለቀቁን አስታወቀ
በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ዛምፋራ ግዛት እየተጓዙ ሳሉ በታጠቁ ኃይሎች ታግተው የነበሩ 33 ሰዎችን ማስለቀቁን የናይጄሪያ ጦር አስታወቀ።
የሰዎቹ መታገት እንደተሰማ ትናንት እሑድ ከሰዓት የአገሪቱ ጦር ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ወደ ዛምፋራ አካባቢ መሰማራቱ ተገልጿል።
ታጣቂዎቹ ታጋቾቹን ወዳልታወቀ ሥፍራ ሊያጓጉዙ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጦሩ ገልጿል።
ጦሩ በታጣቂ ቡድኑ ላይ ተኩስ ሲከፍት ወደ ጫካ ሸሽተው መግባታቸውንም አመልክቷል።
በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ሰዎችን አግቶ ገንዘብ መጠየቅ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
ዋነኛ አውራ ጎዳናዎች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች እና በአንዳንድ ሁኔታዎች መንግሥት የሚፈጽመው ክፍያ ሁኔታውን አባብሶታል።
የናይጄሪያ ጦር ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል አሊዩ ዳንጃ እንደተናገሩት የታጠቁት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ታጋቾቹን ወደየት ለማዘዋወር እየሞከሩ እንደነበር ግልጽ አይደለም።
የአገሪቱ ጦር አጋቾችን ፈልጎ ለማግኘት ጥረቱን ቀጥሏል።
"ጦሩ በስኬታማ ሁኔታ በአካባቢው ተኩስ ከፍቷል። ታጣቂዎቹ ታጋቾቹን ጥለው ወደ ጫካ ሸሽተዋል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ታጋቾቹ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ነጻ መውጣታቸውን አክለዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ንቁ እንዲሆኑ እና ጠቃሚ መረጃ ለደኅንነት ባልደረቦች እንዲሰጡ አሳስበዋል።
የናይጄሪያ ጦር ታጋቾችን በማስለቀቅ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስኬታማ እየሆነ ነው።
ባለፈው ሐሙስ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት በሌላ ጥቃት ታግተው የነበሩ ከ300 በላይ ሰዎችን ማስለቀቅ ተችሏል።
ነጻ ከወጡት መካከል 163 የሚሆኑት ያለፈው ጥር ወር በካውራ ግዛት ከሚገኙት ከዎሮ እና ኑኩ ማኅበረሰቦች የታገቱ ናቸው። ቢያንስ 145 የሆኑት ደግሞ ከኒጀር ግዛት ታግተዋል።
በኦዮ ግዛት ታግተው የነበሩ 44 ተማሪዎች እና መምህራንን ከ50 ቀናት በኋላ ማስለቀቅ የተቻለው ከሳምንታት በፊት ነበር።
ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ለወታደሮች እስከ 80% የደመወዝ ጭማሪ አድርገዋል።
የአገሪቱን ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ለመቀልበስ እየሠሩ ለሚገኙት ወታደሮች "ከፍተኛ አድናቆት" ለማሳየት ያለመ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ወር ለአገሪቱ ጦር የማስፋፊያ ዕቅድ ፈቃድ መስጠታቸው ይታወሳል።
የአገሪቱን ጦር አቅም ለማስፋፋት የተያዘው ዕቅድ የደኅንነት ስጋትን ለመቀልበስ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የማስፋፊያ ዕቅዱ 28,000 ተጨማሪ ወታደሮችን መመልመል እና አራት ወታደራዊ ዕዞችን መጨመርን ያካትታል።
ታጣቂ ኢስላሚስቶች፣ ተገንጣዮች እንዲሁም ንጹኃንን አግተው ገንዘብ የሚጠይቁ ወንጀለኛ ቡድኖች ለአገሪቱ የደኅንነት ስጋት ሆነዋል።
የአገሪቱ አለመረጋጋት በቀጣይ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ዋነኛ አከራካሪ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሆኗል።