ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ሥራ ኤጀንሲ በደረሰበት ጥቃት የምሥራቅ ኢየሩሳሌም ቢሮውን ዘጋ
በጋዛ ከፍተኛ የሰብአዊ እርዳታን የሚያቀርበው የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ሥራ ኤጀንሲ (UNrwa) ለጊዜው የምሥራቅ ኢየሩሳሌም ቢሮውን ለመዝጋት እንደተገደደ ገለጸ።
ኤጀንሲው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በቢሮው ላይ ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው።
የኤጀንሲው ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ “የእስራኤል ነዋሪዎች” በድርጅቱ ግቢ ውስጥ በሚገኙ ንብረቶች ላይ ሁለት ጊዜ እሳት ለኩሰዋል።
በዚህ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ባይኖሩም በንብረት ላይ ግን ውድመት ደርሷል።
“አሁንም የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ሕይወት አደጋ ላይ ነው” ብለዋል ፊሊፔ።
“እሳቱን ሠራተኞቻችን ተረባርበው አጥፍተዋል፤ ምክንያቱም የእስራኤል እሳት አደጋ እና የእስራኤል ፖሊስ ወደ ቦታው ለመድረስ ጊዜ ስለወሰዱ...” ሲሉ ሐሙስ የተከሰተውን ሁኔታ አብራርተዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የእስራኤል ባለሥልጣናት ያሉት ነገር የለም።
ፊሊፔ ላዛሪኒ በማኅበራዊ ገጽ ባጋሩት አንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል በወታደሮች የታጀቡ ሰዎች በዚህ የተባበሩት መንግሥታት ግቢ ሆነው “አቃጥለው! አቃጥለው!” እያሉ ሲጮኹ ያሳያል።
ቢቢሲ ይህን ምሥል ትክክለኛነቱን በራሱ አላረጋገጠም።
ኃላፊው እንደሚሉት እንዲህ ዐይነቱ ትንኮሳ ሲፈጸም ለ2ኛ ጊዜ ነው። በዚህ የተነሳ አስተማማኝ ጥበቃ እስኪኖር ድረስ ቢሮውን ለመዝጋት ተገደናል ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚሰነዘር የገለጹት ኃላፊው ቢሯቸው እርዳታ ለማድረስ እንደተቸገረ ተናግረዋል።
እስራኤል በዚህ የተባበሩት መንግሥታት መሥሪያ ቤት ውስጥ የተሰገሰጉ የሐማስ ሰዎች አሉ ስትል ክስ ማቅረቧ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በርካታ ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ አገራት ልገሳቸውን እንዲያቆሙ አድርጓቸው ቆይቷል።
ይሁንና ይህ ክስ ተጨባጭነት እንደሌለው ካረጋገጡ በኋላ የተወሰኑ አገራት እርዳታ መስጠት ጀምረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ የሆነ ቡድን ባደረገው ምርመራ በዚህ ኤጀንሲ ውስጥ የሐማስ ሰዎች አሉ ለሚለው ክስ እስራኤል “ተጨባጭ መረጃ አላቀረበችም” ብሏል።
ኤጀንሲው በበኩሉ ገለልተኝነቱን እንዲያሳይ፣ የሠራተኞችን ቅጥር ማንነትን የማጣራቱን ሂደት ጠበቅ እንዲያደርግና የአሠራር ግልጽነትን እንዲያሳይ አሳስቧል።