ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኔዘርላንድሷ ልዕልት በደኅንነት ስጋት ከትምህርት ቤት ወጣች
የኔዘርላንድስ ንጉሥ እና ንግሥት የ18 ዓመት ልጃቸው ጥቃት ሊደርስባት ስለሚችል ከአሁን በኋላ በነጻነት መንቀሳቀስ እንደማትችል ገለጹ።
ልዕልት አማሊያ አምስተርዳም ከሚገኘው የተማሪዎች መኖሪያ በመውጣት ዘ ሄግ ወደሚገኘው ቤት ተመልሳለች።
ወላጆቿ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በስዊድን ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ነው በስሜታዊነት ዝርዝር ጉዳዮችን የገለጹት።
ንግሥት ማክስማ “አስቸጋሪውን ሁኔታ” ሲገልጹ ዐይኖቻቸው በእምባ ተሞልቶ ነበር።
“ለእሷ የተማሪነት ሕይወት እንደሌሎቹ ተማሪዎች አይደደለም” ብለዋል።
ልዕልት አማሊያ እና የኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩት ከተደራጁ ወንጀለኞች የተገኘ መረጃ ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክቷል።
ባለፈው ወር በተሰራጨ ኦፊሴላዊ ፎቶ ልዕልት አማሊያን በመጀመሪያ የትምህርት ቀን በፈገግታ ተሞልታ ትታያለች።
ወጣቷ ወደ ተማሪዎች መኖሪያ ቤት መግባቷ እና በአምስተርዳምስ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ፣ በሥነ ልቦና፣ በሕግ እና በምጣኔ ሀብት የመጀመሪያ ዲግሪዋን መማር መጀመሯ በብዙዎች አድናቆት አትርፎላታል።
ታኅሳስ ላይ 19 ዓመት የምትደፍነው አማሊያ ኔዘርላንድስ ውስጥ ብዙዎች በአንፃራዊነት ወደ ኅብረተሰቡ የቀረበች የንጉሣዊ ቤተሰብ ነች ሲሉ ይገልጿታል።
ሞሂቶ የሚባል ፈረስ ያላት ሲሆን፤ በበጋ ወራት በሼቨኒንገን የባሕር ዳርቻ በሚገኝ መጠጥ ቤት ውስጥ መሥራቷ 'የኮክቴይል ንግሥት' የሚል ቅጽል ስም አስገኝቶላታል።
ልዕልት አማሊያ ለ18ኛ ዓመት ልደቷ ባሳተመችው የሕይወት ታሪኳን በያዘው መጽሐፍ ስለ አእምሮ ጤንነቷ ተናግራ ብዙ ጊዜ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን እንደምትጎበኝ ተናግራለች።
የመጀመሪያው የትምህርት ዘመንን በቅጡ ሳታጋምስ ነው የስለላ ተቋም ዘገባን ተከትሎ ልዕልት አማሊያ የምትወደውን እና የሚያስደስታትን የተማሪነት ሕይወት ለመተው የተገደደችው።
የደኅንነት ጥንቃቄዎቹ ጊዜያዊ ብቻ እንደሆኑ ቤተሰቦቿ ተስፋ ያደርጋሉ።
ንግሥት ማክስማ በስዊድን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ልዕልት አማሊያ ነገሩን የተቋቋመችበትን መንገድ እና ለጀግንነቷ ክብር እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የአርጀንቲና ተወላጅና የቀድሞ ኢኮኖሚስት አባቷ አማሊያ አሁንም ዩኒቨርስቲ እንደምትማር ጠቁመው እንዲያውም ጥሩ ውጤት እያስመዘገበች ሊሆን ይችላል በማለት ቀልደዋል።
ንጉሥ ቪለም-አሌክሳንደር እንደ አባት ጉዳዩን እንዲገልጹ ሲጠየቁ “ከባድ ሁኔታ” መሆኑን አምነው ተጽዕኖውን መግለጽ እንዳልቻሉ ተናግሯል።
ለንጉሣዊው ቤተሰብ አባላት ወይም ለመንግሥት ባለሥልጣናት ስለደኅንነት ጉዳዮች ማውራት አልተለመደም።
ፖሊስ፣ የሕዝብ ዐቃቤ ሕግ እና የመንግሥት ሚኒስቴር በንጉሣዊያኑ ጥንዶች መግለጫ ላይ አስተያየት ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም።