ቴይለር ስዊፍትን እና መስክን የመሰሉ ታዋቂ ሰዎችን አውሮፕላኖች እየተከታተለ የሚያስጨንቀው ተማሪ

ታትሟል

ፍሎሪዳ ያለ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የዓለማችን ቅንጡ ሀብታሞችን እና ታጣወቂ ሰዎችነe እያስጨነቀ ነው። እንዴት?

ነገሩ ወዲህ ነው። ይህ ተማሪ የእነዚህ የበርካቶች መነጋገሪያ የሆኑ ሰዎች የግል አውሮፕላኖች ከየት ተነስቶ የት አረፈ? የሚለቀውስ በካይ ጋዝ (ካርበን) ምን ያህል ነው? የሚለውን እየተካታተለ ይፋ ያደርጋል።

ጃክ ስዊኒ ይባላል። “እመኑኝ አንዳንድ የቴይለር ስዊፍት ሙዚቃዎችን እወዳቸዋለሁ” ይላል።

ምንም እንኳ ስዊፍት ይህን ተማሪ ከስሼ አስቀፈድደዋለሁ ብላ ብታስፈራራም፤ የግል አውሮፕላኗ ከየት ተነስቶ የት አረፈ የሚለውን የማወቅ መብት አለን ይላል።

“ፍትሐዊ መሆን እፈልጋለሁ” ይላል ለቢቢሲ በላከው ኤሜይል። “ማንም ይሁን ማን መረጃቸውን ከማጋራት ወደኋላ አላልም።”

ትኩረቱ ቱጃር እና ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች የግል አውሮፕላን መነሻ እና መድረሻ ነው። ይህን የሚያጋራው በማኅበራዊ ሚድያ ገጾቹ ነው።

ይህን ተከትሎ የ21 ዓመቱ ወጣት የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ “እንከስሃለን” የሚሉ ማስፈራሪያዎች ይደርሱታል።

የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያ እና የአስተማሪ ልጅ የሆነው ጃክ ኦርላንዶ ነው ያደገው።

ለአቪየሽን እና ቴክኖሎጂ ልዩ ፍቅር እንዳለው የሚናገረው በተለይ ደግሞ የኢላን መስክ ኩባንያ የሆኑት የስፔስኤክስ እና ቴስላ አድናቂ ነው።

ይህንን ፍላጎቱን ተከትሎ ነው ዘኤርትራፊክ.ኮም [TheAirTraffic.com] የተባለ የአውሮፕኖችን መግቢያ እና መውጫ የሚከታተል ድረ-ገፅ የሠራው።

የማኅበራዊ ሚድያ ገፆቹ ደግሞ ታዋቂ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ጉምቱ የቴክኖሎጂ ሰዎች እና የሩሲያ ባለሀብቶች የግል አውሮፕላንን ይከታተላል።

መረጃውን የሚያገኘው ለሕዝብ ጥቅም ይፋ ከሆኑ የመረጃ ቋቶች ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ እኒህን መረጃዎች የሚሰበስቡ ሰዎች ብዙ ልምድ የሌላቸው ወጣቶች ናቸው።

ሰማይ ላይ ያሉ አውሮፕላኖች ያሉበትን ቦታ የሚጠቁም መረጃ የሚልኩ ሲሆን፣ እኒህን መረጃዎች የሚሰበስቡ መሣሪያዎች በቀላሉ መግዛት ይቻላል።

በእንግሊዝኛው ኦሲንት አሊያም ኦፕን ሶርስ ኢንተለጀንስ የተባለ የበይነ-መረብ ማኅበረሰብ መሰል መረጃዎችን በማጋራት ይታወቃል።

እኒህ ሰዎች ብዙዉን ጊዜ ለሕዝብ ይፋ የሆነ መረጃ ተጠቅመው አስገራሚ፣ ዕውቀት የሚያስጨብጡ አሊያም አዝናኝ የሆኑ ይዘቶችን እና መረጃዎችን ያጋራሉ።

እንዲሁ መረጃን ማጋራት ከሚወዱ ሰዎች ጀምሮ ሥራችን ብለው ጥናት የሚያካሄዱ ባለሙያዎች እና የምርመራ ጋዜጠኞች ይህን መላ ይጠቀማሉ።

“ይህን የጀመርኩት እንዲሁ ስለመሰጠኝ ነው” የሚለው ጃክ የሴንትራል ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የዲግሪ ተመራቂ ተማሪ ነው።

“በግልፅነት እና መረጃን ለሕዝብ በማድረስ አምናለሁ” ይላል ጃክ።

ቀስ በቀስ የግል አውሮፕላኖች ምድራችን ላይ ስለሚያደርሱት ጉዳት መመዝገብ ያዘ። “አብራሪዎቹ ስለ ካርበን ልቀት የሚያሳየውን መረጃ ለመደበቅ እየሞከሩ ነው” በማለት ይተቻል።

ቴይለር ስዊፍት እና አጃቢዎቿ በሚያደርጉት በረራ እያደረሱ ያሉትን የካርበን ልቀት የሚያሳይ አንድ ጥናት የተሠራው የጃክን መረጃ መሠረት አድርጎ ነው።

ዘፋኟ የሙዚቃ ድግስ ለማቅረብ ባደረገቻቸው ሁለት በረራዎች የካርበን ልቀትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ መግዛቷን ትናገራለች።

ነገር ግን የቴይለር ስዊፍት ጠበቃዎች እንደሚሉት ጃክ የሚለቀው መረጃ የዘፋኟን ግላዊ መብት የሚገፍ እና አደጋ ላይ ሊጥላት የሚችል ነው።

ጠበቃዎቹ ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ በለጠፉት ደብዳቤ የአውሮፕላን መውጫ እና መግቢያን መከታተል “የሞት እና የሕይወት ጉዳይ ነው” አልፎም “ለመከታተል፣ ጥቃት ለማድረስ አሊያም ቁጥጥር ለማድረግ ካልሆነ በቀር” ይህን መረጃ ማጋራት ምንም ጠቀሜታ የለውም ሲሉ ይከራከራሉ።

ጃክ፤ እኒህን ክሶች አይቀበልም። ሕዝቡ የፖፕ ኮከቧ አውሮፕላን ከየት ተነስቶ የት ደረሰ የሚለውን ማወቅ ይሻል ይላል።

“የዘፋኟ አድናቂዎች ቴይለርስዊፍትጄትስ የሚል የማኅበራዊ ሚድያ ገጽ አላቸው፤ ይህ ምስክር መሆን ይችላል” ሲል ምላሽ ይሰጣል።

ወጣቱ አክሎም ታዋቂ ሰዎች ሕዝብ ባለበት ሥፍራ ሊገኙ ይችላሉ ወይስ አይችሉም? የሚለውን ማወቅ ሰዎች ይሻሉ የሚል መከራረከሪያ ያቀርባል።

ቴይለር ስዊፍት ቅዳሜ ምሽት ቶኪዮ የሙዚቃ ድግስ [ኮንሰርት] ነበራት። እሑድ ደግሞ ላስ ቬጋስ ፍቅረኛዋ የሚጫወትበት ሱፐር ቦውል የተሰኘው የአሜሪካ ፉትቦል ፍፃሜ ይካሄዳል።

አውሮፕላን የሚከታተሉ ድረ-ገፆች በረራው ከየት ተነስቶ የት ደረሰ የሚለውን እንጂ ውስጥ ማን አለ? ወርደውስ የት ሄዱ? የሚለውን ይፋ አያደርጉም።

ጠበቃዎቿ ግን በቅርቡ አንድ ግለሰብ ኒው ዮርክ ወደ ሚገኘው ቤቷ ለመግባት ጥረት ሲያደርግ በፖሊስ መያዙን እንደምሳሌ ጠቅሰው፤ ይህን መረጃ ተጠቅመው ሰዎች የት እንደገባች፣ እንደወጣች ማወቅ ይችላሉ ይላሉ።

ጃክ ለቴይለር ስዊፍት ምክር አለው። ዘፋኟ ይህ መረጃ ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን የምትፈልግ ከሆነ የልደት ቀን እና ስሟን የማያካትት የይለፍ ቃል መርጣ የግል አውሮፕላኖቿን መረጃ መደበቅ ትችላለች።

የጃክ ጠበቃ ጄምስ ስላተር፤ ቴይለር ስዊፍት ክስ ትመሠርታለች ብለው እንደማያስቡ ሲናገሩ “ምንም ያጠፋው ጥፋት የለም” ይላሉ።

አንዳንዶች በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው ለጃክ ድጋፋቸውን ሲገልጡጹ፣ ሌሎች ደግሞ “ቴይለር ስዊፍት እንደ ልዕልት ዳያና እንድትሞት ይፈልጋል” ሲሉ ይወቅሱታል።

ተመራቂው ተማሪ ከታዋቂ ሰዎች ጫና ሲደርስበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ኢላን መስክ በአውሮፓውያኑ 2022 ትዊተርን [አሁን ኤክስ የተሰኘው] ሲገዛ የመናገር ነፃነትን ዋቢ አድርጎ የጃክን ገጽ እንደማይዘጋ ተናግሮ ነበር።

ነገር ግን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ መስክ ቃሉን አጥፎ የጃክን ገጽ ከዘጋ በኋላ ክስ እንደሚመሰርት ዝቷል።

ይህን ያደረገው ቢሊየነሩን የሚከታተል አንድ ግለሰብ የኢላን መስክ ህጻን ልጅ ውስጥ እያለ ወደ አውሮፕላኑ ገብቶ በገላጋይ ከወረደ በኋላ ነው።

ነገር ግን ፖሊስ ይህን ያደረገው የራሱ የኢላን መስክ ጠባቂ የሆነ ግለሰብ እንጂ የጃን ገጽ ከዚህ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ይላል።

አሁን ጃክ የኢላን መስክ የግል አውሮፕላን መነሻ እና መድረሻን ከ24 ሰዓታት በኋላ ይፋ ያደርጋል።

በተለያዩ የማኅበራዊ ሚድያ ገጾቹ መረጃ የሚያጋራው ጃክ፤ ኪም ካርዳሺያን፣ ጄፍ ቤዞስ፣ ቢል ጌትስ፣ ማርክ ዛከርበርግ፣ ዶናልድ ትራምፕ እና የሌሎችንም ታዋቂ ሰዎች አውሮፕላኖችን ይከታተላል።

ፌስቡክ እና ኢንስታግራም የቴይለር ስዊፍትን የግል አውሮፕላን መረጃ የሚያጋራበትን ገጽ ዘግተውበታል።

ሜታም ሆነ የቴይለር ስዊፍት ጠበቃዎች ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አልፈቀዱም።