ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሞቃዲሾ እስከ ኢትዮጵያ ጥቃት የሚፈጽመውን አልሻባብ የሶማሊያ መንግሥት ያሸንፈዋል?
የሶማሊያ አዲሱ መንግሥት በቅርቡ አስደናቂ ሹመት ሰጥቷል። በአንድ ወቅት የታጣቂው ቡድን የአልሸባብ አመራር የነበረው ግለሰብ ማዕከላዊው የሶማሊያ መንግሥት በካቢኔ ውስጥ አካቷል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ደግሞ በአንድ ሆቴል ላይ ሞቃዲሾ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች የሚጠብቃቸውን ከባድ ሥራ የሚያስታውስ ነው።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ በግንቦት ወር ሥልጣን ተረከቡ። 15 ዓመታት ያስቆጠረውን እስላማዊውን አማጺ ቡድንን ማስቆም ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን አወጁ።
ሦስት ወራት እንዳለፉም አልሸባብ በዋና መዲናዋ ሞቃዲሾ፣ ከፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት አለፍ እንዳሉ የሚገኝን ሆቴል በመውረር አስደንጋጭ ጥቃት ፈጸመ።
የአልሻባብ ታጠቂዎች ለ30 ሰዓታት ተቆጣጥረውት በቆዩት ሃያት ሆቴል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ 117 ደግሞ ቆስለዋል ብለዋል ባለሥልጣናት።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቡድኑ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ወረራ በጎረቤት ኢትዮጵያ ላይ ፈጽሟል።
ቡድኑ ለአዲሱ ፕሬዘዳንት ያለውን ንቀት ያሳየ ይመስላል።
ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ይህን ውስብስብ የተቀናጀ ጥቃት “ጨዋታ ቀያሪ” ሲሉ ገልጸውታል። ለማቀድ ቢያንስ 18 ወራት የፈጀ እና በግምት 1,200 ተዋጊዎችን ያሳተፈ ነው።
በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ስቴፈን ታውንሴንድ፣ ታጣቂዎቹ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው እስከ 150 ኪሎ ሜትር ዘልቀው መግባታቸውን ተናግረዋል።
ቡድኑ ይህንን ጥቃት ለመሰንዘር የቻለበት አንዱ ምክንያት በኢትዮጵያ ለዓመታት ከታየው መረጋጋት እና ዕድገት በኋላ ግጭት በመጨመሩ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀስቅሶ ብዙም ሳይቆይ የአልሸባብ አባል ደወለልኝ ስትል የቢቢሲዋ ሜሪ ሃርፐር ትገልጻለች።
“እጆቻችንን አጣጥፈን ኢትዮጵያ ራሷን እያጠፋችበት ያለውን ትርኢት እያየን እየተደሰትን ነው። ዋናው ጠላታችንን የምንመታበት ጊዜ በመጨረሻም እየቀረበ ነው” አለኝ።
የሶማሊያ መንግሥትን በመደገፍ ወታደሮቿን ከላከች የቀጣናው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። እአአ በ2012 የመጀመሪያውን የሥልጣን ዘመናቸውን በጀመሩ ማግስት በሰጡት ቃለ መጠይቅ በሁለት ዓመት ውስጥ ታጣቂዎቹን እንደሚያሸንፉ ተናግረው ነበር።
ከአሥር ዓመታት በኋላም ቡድኑ ጥንካሬውን ይዞ እንደቀጠለ ነው።
መቀመጫውን በሞቃዲሾ ያደረገውና የሂራል የተሰኘው የደኅንነት ተቋም ሊቀመንበር መሐሙድ ሙባረክ “[ቡድኑ] እአአ በ2012 ከነበረበት የበለጠ ኃይለኛ እና የተራቀቀ ሆኗል” ብለዋል።
አልሸባብ ትይዩ መንግሥት በማቋቋም ሰፊ ቦታዎችን ተቆጣጥሯል።
በሚቆጣጠረው ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም ግብር ይሰበስባል። የሞቃዲሾ ነዋሪዎች እንኳን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ይልቅ የቡድኑን የፍትህ ሥርዓትን ይመርጣሉ። የበለጠ ቀልጣፋ እና በሙስና የተዘፈቀ አይደለም ብለው ያምናሉ።
ቡድኑ እንዳሻው ማጥቃቱን ቀጥሏል። በፓርላማ ላይ ሞርታሮችን በመተኮስ ኤምባሲዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የውጭ ወታደሮች ወደሚገኙበት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያም ጥቃቱን ይሰነዝራል።
አልሸባብ የአልቃይዳ በጣም ስኬታማው አጋር ተብሎ መገለጹ ምንም አያስደንቅም።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ አልሸባብን በኃይል ማሸነፍ እንደማይቻል አምነዋል።
እአአ ነሐሴ 2 መንግሥት ግጭቱን የማስቆም አዲስ ስልት አካል አድርጎ በማሰብ ከቀድሞ ጠላቶቹ አንዱን ወደ ካቢኔው በመቀላቀል ድፍረት የተሞላ ውጤቱ ያልታወቀ ውሳኔ አድርጓል።
ሜሪ ሃርፐር እንደምትለው “እኔ በወቅቱ ሞቃዲሾ ነበርኩኝ። መንገድ በመዘጋቱ ከጓደኞቼ ጋር መኪና ውስጥ ተቀምጠን ነበር።”
ማንም ከመኪናው እንዲወጣ መታዘዝ፣ ተሽከርካሪ እና ቦርሳዎች ስለመፈተሻቸው የተጨነቀ አልነበረም።
“ወዳገኘነው አነስተኛ ጥላ ሄደን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃል አቀባይ አዲሱን ካቢኔ ሲያበስር ለማየት ተንቀሳቃሽ ስልካችን ላይ ዓይኖቻችን ተጣበቁ።”
ሲጠብቁት የነበረው ስም በአፍጋኒስታን የሰለጠነው የአልሸባብ መስራች አባልን ነው።
ወሬው እውነት ሆኖ አረፈው።
የአልሸባብ የቀድሞ ምክትል መሪ እና ቃል አቀባይ ሙክታር ሮቦው የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።
አንዳንዶች በድርጊቱ ተደናገጡ። ብዙ ሶማሊያውያን ያሉበትን ለጠቆመ አምስት ሚሊዮን ዶላር አሰጣለሁ ስትል በአንድ ወቅት አሜሪካ ገልጻው የነበረው ግለሰብ ወደ የካቢኔ አባል መሆናቸውን በደስታ ተቀብለዋል።
ከእነዚህ መካከል ከአምስት የአልሸባብ ጥቃቶች የተረፈው የሕዝብ እንደራሴ እና የቀድሞ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሞአሊሙ መሐመድ ይገኝበታል። በፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ በደረሰ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ሕይወቱ ለጥቂት ተርፋለች።
“የሮቦውን ሹመት እቀበላለሁ” ይላል መሐመድ።
“የቀድሞ የጂሃዲስት መሪ እንደመሆኑ ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር አክራሪ አስተሳሰቦችን ከመቃወም ባለፈ ታጣቂዎቹ ትክክለኛውን የኢስላም መንገድ አለመከተላቸውንም የማሳመን አቅም አለው።”
ሮቦው እአአ በ2013 ነበር ከአልሸባብ ጋር ግጭት ውስጥ የገባው። ቡድኑንም በአደባባይ አወገዘ። በኋላም ጥቅምት 2017 በሞቃዲሾ በደረሰው ጥቃት ለተጎዱ ደም ለገሰ። በዚህ ከባድ የመኪና ፍንዳታ 600 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።
እአአ ታኅሣሥ 2018 ተይዞ ሚኒስትር ሆኖ እስኪሾም ድረስ የቁም እስረኛ ሆኖ ቆይቷል። በእስር ላይ እያለ የስልክ ጥሪ እንደደረሰው ተናግሯል።
የደኅንነት ባለሙያ የሆኑት ሙባረክ እንደሚሉት ከሆነ የሮቦው ሹመት “ከፀረ-ሽብርተኝነት አንፃር ድንቅ ሃሳብ ነው።”
"በተለይም ከርዕዮተ ዓለም አንጻር ትልቅ መሳሪያ ነው። ምክንያቱም በአልሸባብ ላይ ጠንካራ የአስተምህሮ ግፊቶችን ያሳድራል። የቡድኑ መስራች አባል በመሆኑም አብጠርጥሮ ያውቃቸዋል። እንዴት እንደሚያስቡ እና እንዴት እንደሚሰሩም ያውቃል።"
ሌሎች ደግሞ ሹመቱን አውግዘው ምላሽ ሰጥተዋል። በሶማሊያ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀው ግጭት ያስከተለው ሌላ ምልክት አድርገው ይመለከቱታል።
ሹመቱን በሚመለከት ማኅበራዊ ሚዲያዎች በትችት ተጥለቅልቀዋል። በትዊተር ላይ የተሰጡ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች አስከፊ ነበሩ። ጥቂቶቹን እንመልከት፡
“ሶማሊያ ጠንካራ አስተዳደር ቢኖራት ኖሮ ሮቦው በአደባባይ ይገደሉ ነበር።”
“የዚህ ጨካኝ እና ክፉ ገዳይ መሾም አንድ ነገር ብቻ ያሳያል፣ አልሸባብ የሶማሊያ መንግሥት ውስጥ በይፋ ሰርጎ መግባቱን።”
አል-ሸባብ የቀድሞ ምክትል መሪው የመንግሥት ሥራን መቀበሉ እጅግ አሰቃቂ ወንጀል ነው ብሎ ያምናል። የመጨረሻው ከባድ ቅጣት ይገባዋልም ይላል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ አሊ ዴሬ ተቀርጾ በተላለፈ የ10 ደቂቃ መግለጫው “ሮቦ ከሃዲ ነው። ደሙን ማፍሰስም ተፈቅዷል” ብሏል።
ፕሬዝደንት መሐሙድ ሹመታቸው ከተደራጀ ወታደራዊ ጥቃት ጋር ተደማምሮ አልሸባብን በማዳከም ወደ ንግግር እንዲገባ እንደሚያስገድደው ያምናሉ።
ሙባረክ ግን “ሁሉም በፖለቲካ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው” ብለዋል።
“አልሸባብ የሚወድቀው የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች የውጭ ኃይሎች፣ የፌደራል እና የክልል ወታደሮች እና የአካባቢ ታጣቂዎች አንድ ላይ ሲሰባሰቡ ብቻ ነው። ያኔ ነው ተደራድረው መግባባት የሚችሉት” ይላሉ።
የቡድኑ አባል የነበሩት እና ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሮቦው አሁን ስለ ሰላም እና ይቅርታ ይሰብካሉ። ከእስልምና ሊቃውንት ጋር በመስራት የሚሰሩት ፀረ እስላማዊ መሆኑን በማሳመን ሰዎች ከአልሸባብ እንዲወጡ እሠራለሁ ብለዋል።
የመንግሥት ቁማር ስለመሳካቱ ወይም አልሸባብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለመታገል ያለውን ቁርጠኝነት ያጠናክራል የሚለው ነገር ለጊዜው ግልጽ አይደለም።
የቅርብ ጊዜ ክስተቶች የሚጠቁሙት ግን የኋለኛው እንደሚሆን ነው።