የሶማሊያ ጦር ለ30 ሰዓታት የፈጀው የሆቴል ከበባ ማብቃቱን አስታወቀ

ታትሟል

የሶማሊያ ጦር በመዲናዋ ሞቃዲሾ የሚገኘውን ሆቴል ጥሰው ገብተው ይዘው የነበሩ ታጣቂዎችን ድል ማድረጉን አስታወቀ።

በዚህ ጥቃት 12 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የነበረውም ከበባ ለ30 ሰዓታት መቆየቱም ተነግሯል። የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ታጣቂዎቹ አርብ እለት ወደ ሞቃዲሾ ሃያት ሆቴል ለመግባት ፈንጂዎችን የተጠቀሙ ሲሆን ከዚያም ሆቴሉን መቆጣጠራቸውንና  የሆቴሉ እንግዶችንም አግተው ነበር።

ለዚህ ጥቃት ጽንፈኛው አል ሻባብ ሃላፊነቱን ወስዷል።

"የጸጥታ ሃይሎች ከበባውን አሁን አስቁመዋል፤ ታጣቂዎቹም ሞተዋል። በአሁኑ ወቅት ከሆቴሉም ምንም አይነት የተኩስ ድምጽ እየተሰማ አይደለም። “ሲሉ ስማቸው ያልጠቀስ አንድ ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

የጸጥታ ኃይሎች አርብ ምሽት እና ቅዳሜ ባደረሱት ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት ሆቴሉ በአብዛኛው ወድሟል። ከስፍራው የወጡ ቪዲዮዎች  ፍንዳታዎች እና ከሆቴሉ ህንጻ ሰገነት ላይ ጭስ ሲወጣም ታይቷል።

የሶማሊያ ጦር ጥቃቱ ማክተሙን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ቢቢሲ በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልቻለም።

አንድ የፖሊስ መኮንን ለሮይተርስ እንደገለጹት ታጣቂዎች ሆቴሉን አርብ አመሻሽ ላይ ጥሰው ለመግባት ሁለት ፈንጆችን መጠቀማቸውን ተናግረዋል።

መጀመሪያ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ከአል ሻባብ ጋር ግንኙነት ያለው ድረ- ገጽ እንዳስታወቀው “የታጣቂዎች ቡድን ሆቴሉን በኃይል ጥሰው ከገቡ በኋላ በዘፈቀደ እየተኮሱ ነው” በሚል አስፍሯል። ዘገባው ጨምሮም የፌደራል መንግሥት ሰራተኞች የሚገናኙበት ታዋቂ ቦታም ነው ይላል።

"እስካሁን 12 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠናል" ሲሉ መሃመድ የተባሉና የአባታቸው ስም ያልተጠቀሰ የደህንነት ሰራተኛ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን አግተው የነበሩት ታጣቂዎቹ መተለላፊያ ደረጃዎችን በቦምብ አፈራርሰዋቸው ስለነበር የጸጥታ ሃይሎች ለሰዓታት ያህል እንግዶች ያሉበት ስፍራ ለመድረስ ሲቸገሩ ነበር።

የሞቃዲሾ ድንገተኛ ሆስፒታል ዳይሬክተር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩ በሆቴሉ ጥቃት ቢያንስ 40 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።

የአልቃይዳ አጋር የሆነው አል ሻባብ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጦርነት ውስጥ ገብቷል።

ቡድኑ አብዛኛውን የደቡብ እና መካከለኛውን ሶማሊያን ይቆጣጠራል፣ ነገር ግን መቀመጫውን ሞቃዲሾ ባደረገው መንግሥት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ተጽእኖ መፍጠር ችሏል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ድንበር ጥቃቶችን የፈጸሙ ሲሆን ይህም በአል ሻባብ አዲስ የጥቃት ስትራቴጂ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በግንቦት ወር ከተመረጡ በኋላ በቡድኑ ዋና ከተማው አርብ ላይ የደረሰው ጥቃት የመጀመሪያው ነው።